




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ የ2017 ዓ.ም ሀገራዊና ክልላዊ የፈተና አስተዳደር ሥርዓት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በቦንጋ ከተማ ተገምግሟል።
በክልሉ በ2017 የትምህርት ዘመን በሀገር አቀፍ ፈተና 19 ሺህ 1 መቶ 27 እና 38ሺህ 5 ነቶ 93 ክልላዊ ፈተና በድምሩ 57 ሺህ 7 መቶ 20 ተማሪዎች እንደሚወስዱ ተጠቁሟል።
የክልሉ የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ነጋ አበራ በምክክር መድረኩ እንደተናገሩት፤ በትምህርት ዘርፍ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች በዘርፉ ያጋጠሙ ስብራቶችን ለመጠገን አቅም ሆኗል ብለዋል።
ይሄው ተግባር በየደረጃው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ጠቅሰው የፈተና አስተዳደር ሥርዓቱን በማዘመን በሂደቱ የሚፈጠሩ ማነቆዎችን ማስቀረት እንደሚጠበቅ ነው ያብራሩት።
የበይነ መረብ የፈተና አሰጣጥ ሥርዓቱን ቀጣይ በሁሉም አከባቢዎች እንዲሰጥ በአስፈላጊ ጉዳዮች ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም የገለፁት አቶ ነጋ አበራ በዘርፉ ስርነቀል ለውጥ ለማምጣት የምዘና ስርዓቱን ለማዘመንና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በየደረጃው የሚገኙ መዋቅሮች አስፈላጊ ሀብት መመደብና ያለውን የሰው ኃይል አሟጦ መጠቀም ያስፈልጋልም ብለዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማዉ ዘዉዴ በበኩላቸው በዘንድሮው ሀገራዊ እና ክልል ዓቀፍ ፈተናዎች ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ለማስቻል የሚመለከታቸው ሁሉ ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
በቀሪ ጊዜያት የፈተና አስተዳደር ሥርዓቱ ውጤታማ ለማድረግ ከሚከናወኑ ተግባራት ጎን ለጎን በትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ለፈተና አካላዊ እና ስነልቦናዊ ዝግጅት እንዲያደርጉ ትኩረት ይደረጋል ነው ያሉት።
በክልሉ ፈተናውን በበይነ መረብ እና በወረቀት የሚወስዱ ተማሪዎችን የመለየት ሥራ መሰራቱን የጠቆሙት አቶ አልማው ተማሪዎች ለፈተና የሚጓጓዙበት ትራንስፖርት ከወዲሁ ማዘጋጀት እና መሰል ተግባራትን ማከናወን ያስፈልጋል ብለዋል።
የምክክሩ ተሳታፊዎችም የፈተናውን ሂደት በተቀመጠ አግባብ ውጤታማ ለማድረግ የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ ገልፀዋል።
በፍቅር ከበደ
