




“የጤና ዘርፍ አርበኝነት ለሀገር ዕድገት” በሚል መሪ ቃል በዞኑ ከሚገኙ የጤና ባለሙያዎች፣ ሠራተኞች እና ከባለድርሻ አካላት ጋራ የምክክር መድረክ በዞን ማዕከል እየተካሄደ ይገኛል።
በምክክር መድረክ የተገኙ የዳዉሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ እንደገለጹት የጤናው ዘርፍ ለሀገር ዕድገትና በሁሉም መስክ ሁለተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና አለው ።
የጤና ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን በማሻሻል ከማኅበረሰብ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ማነቆችን በዘለቂነት ለመፍታት የሙያው ሥነምግባርንና የህዝብ አደራን ሊወጡ እንደሚገባም አስተዳዳሪው ገልፀዋል።
የዳዉሮ ዞን ጤና መምሪ ኃላፊ አቶ አስራት ቸርነት በበኩላቸው በጤናው መስክ የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማስቀጠልና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ለመሻገር የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት ተዘርግቶ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የጤናው ዘርፍ ለሀገራችን ሁለተናዊ ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የጎላ ነው ያሉት ኃላፊው የጤና አገልግሎት አሰጣጥ እየተሻሻለ እንደሚገኝና በርካታ ስኬቶች በጤናው ዘርፍ እየተመዘገቡ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
የጤና ባለሙያዎች የዜጎችን ጤና በመጠበቅ፣ ጤናን በማበልፀግ፣ በሽታን በመከላከል፣ አክሞ በማዳን እና ተሀድሶ አገልግሎት በመስጠት የህይወት አድን ስራ ሲሰሩ መቆየታቸውን አስታውሰው በቀጣይም የተጣለባቸውን ኃላፊነት በተገቢው እንዲወጡም አሳስበዋል ሲል የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።
