ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ) የክልሉን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ለማፋጠን ያለመ ዉይይት ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር አካሄዱ

Spread the love

ውይይቱ የመሶብ ማዕከላትን፣ የዲጂታል መታወቂያንና የኢ-ቲኬት አገልግሎትን እንዲሁም የፋይዳና የ5 ሚሊየን ኮደርስ ለማስፋፋት ትኩረት አድርጓል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ከኢትዮ-ቴሌኮም ዋና መሥሪያ ቤትና ከጂማ ዲስትሪክት ከመጡ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

ውይይቱ የክልሉን የዲጂታል ሽግግር እውን ለማድረግ በቀጣይ በጋራ ሊሰሩ በሚገባቸው ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነዉ። በዚህም የኢትዮ-ቴሌኮም የባለሙያዎች ቡድን ለክልሉ አመራሮች ባቀረበው ገለጻ፣ የክልሉን አገልግሎት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩ ሀሳቦችን አቅርበዋል።

በክልሉ ከተሞች እየተገነቡ ያሉትን የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶችን በዘመናዊ የኔትወርክ ሲስተም በማስተሳሰር ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት፣በትራንስፖርት ዘርፍ ያለውን እንግልት ለመቀነስ ዘመናዊ የኢ-ቲኬት አገልግሎት ማስጀመር፣የክልሉን መረጃዎች በአንድ ማዕከላዊ ቋት (Data Center) በማስቀመጥ ደህንነቱ የተጠበቀና ፈጣን የመረጃ ፍሰት መፍጠር እና ለስብሰባና ውይይቶች የሚወጣውን ወጪና ጊዜ ለመቆጠብ የሚያስችል የቪዲዮ ኮንፈረንስ አገልግሎት በክልሉ ማስፋፋት ዉይይቱ ያተኮረባቸዉ ጉዳዮች ናቸዉ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በበኩላቸው፣ የክልሉ መንግስት ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የሰጠውን ትኩረት አጽንኦት ሰጥተዋል። በተለይም የኔትወርክ መቆራረጥና የአቅም ውስንነት ለቪዲዮ ኮንፈረንስ እና ለሌሎችም የዲጂታል አገልግሎቶች ትልቅ እንቅፋት መሆኑን አንስተው፣ ኢትዮ-ቴሌኮም ለመሰረተ ልማት ዝርጋታ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል።

በተጨማሪም በክልሉ እየተሰጠ ያለውን የ5 ሚሊዮን ኢትዮ-ኮደርስ ስልጠናና በዚህ በጀት ዓመት 1.9 ሚሊዮን ዜጎችን የዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ ለማድረግ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ተጨማሪ የመመዝገቢያ ኪቶች እንደሚያስፈልጉ ገልጸው፣ አገልግሎቱ የገጠሩን ማህበረሰብ እንዲያዳርስ በትብብር መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና መስሪያ ቤት ከፍተኛ የስራ ኃላፊ አቶ ዮናታን አፊራሳ በበኩላቸው፣ ተቋሙ በክልሉ የሚነሱ የኔትወርክ ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል። የመሰረተ ልማት ዝርጋታውንም ከክልሉ መንግስት ጋር በቅንጅት በማከናወን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እንደሚሰራ ቃል ገብተዋል።

ውይይቱ የክልሉን የዲጂታል ሽግግር እውን ለማድረግ የጋራ መግባባትና ጠንካራ የትብብር መንፈስ የተፈጠረበት ሲሆን፣ በቀጣይ የተሻለ ዉጤት ለማስመዝገብ በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ ተደርሷል።

በተከተል ወ/ሚካኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *