በክልሉ ለኦዲት ግኝቶች ምላሽ በማይሰጡ ተቋማት ላይ የተጠያቂነትና ህግ የማስከበር ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፦ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የኦዲት ግኝት አስመላሽ ግብረ-ሀይል በኦዲት ግኝት እርምት አወሳሰድ ላይ የአፈፃፀም ግምገማ መድረክ በቦንጋ ከተማ አካሂዷል፡፡

በመድረኩ በክልሉ በቤንች ሸኮና በካፋ ዞን በንግድና ኢንቨስትመንት እና በስራ ክህሎትና ኢንተርፕራይዝ መምሪያ የተደረገውን የክዋኔ እና አካባቢ ኦዲት ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጓል፡፡

የክልሉ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ዋና ኦዲተር አቶ አስራት አበበ ባቀረቡት የሥራ ዕድል ፈጠራ የኦዲት ሪፖርት እንደገለጹት፥ በክልሉ የመንግስትን ውስን ሀብት ከብክነት ለመጠበቅ ህጋዊ አሰራሩን ተከትሎ ስለመፈፀሙ ለመከታተልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ስራዎች መከናወኑንና በክልሉ በቤንች ሸኮና በካፋ ዞን የክዋኔና አካባቢ ኦዲት ስራዎችን መሰራቱን አስታውቀዋል።

በበጀት ዓመቱ ኦዲት ከተደረጉ አንዳንድ መስሪያ ቤቶች ለተገኙ ለኦዲት ግኝት ምላሽ ከመስጠት አኳያ ዳተኝነት መኖሩን ገልፀው የኦዲት ግኝቶችን በዘላቂነት ማስተካከልና በኦዲት ግኝት ላይ በተስተዋሉ የአሰራር ክፍተቶች ላይ እርምጃ መውሰድ ሊጠንከር እንደሚገባ አመላክተዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ክቡር አቶ ወንድሙ ኩርታ በ2017 በጀት ዓመት በቅንጅት በርካታ ስራዎች መሠራታቸውን ያነሱት ሲሆን በተለይም የክልሉ ኦዲት አስመላሽ ግብረ-ሀይል ውይይት እና ስብሰባ ከማድረግ ባሻገር አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ እና እስከታች ዞኖች ድረስ በመውረድ እጅግ በጣም ውጤታማ ተግባር መከናወን መቻሉን ገልፀዋል፡፡

ዋና አፈጉባኤ አክለውም ግብረ-ሃይሉ በ2017 ዓ.ም በፋይናንሻል ኦዲት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራቱን ጠቁመው በክልሉ ኦዲት ከተደረጉ አንዳንድ መስሪያቤቶች በርካታ ንብረት ያለአግባብ የባከነ ሀብትና ንብረት የማስመለስ እና የፋይናንስ አሰራር ስርዓት ማስጠበቅ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

በክልሉ ከሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ከኦሞ ባንክ እና አከባቢ ህግ ተገዥነት አንፃር መሠረታዊ ችግሮች መኖሩንና በቀጣይም ኦዲት ተደርጎ ለተሰጡ ለኦዲት ግኝቶች ምላሽ በማይሰጡ ተቋማት ላይ የተጠያቂነትና ህግ የማስከበር ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ዋና አፈጉባኤ አቶ ወንድሙ ገልፀዋል፡፡

የክልሉ ምክር ቤት የኦዲት እና የፋይናንስ ጉዳዮች ቋም ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ የኋላሸት በላይነህ በበኩላቸው የኦዲት ስራችን ጠንከራ እና ቀልጣፋ ከማድረግ ባሻገር የተገኙ የኦዲት ግኝቶች በማስመለሱ ላይ ሁሉም የግብረ-ሃይሉ አባላት ኃላፊነት ወስደው መስራት እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

የክልሉ ኦዲት አስመላሽ ግብረ-ሃይል ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ በ2017 ዓ.ም ተቋማት በኦዲት ግኝት ላይ ምላሽ መስጠት ከነበረበት 6.3 ከመቶ ወደ 78 ከመቶ አፈፃፀም ማስመዝገብ መቻሉንና በተያዘው 2018 በጀት ዓመት በክልሉ በክዋኔ ኦዲት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራ መሆኑን የጠቀሱት ቋም ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ የኀለሸት የኦዲት ስራ ለአንድ ለተወሰነ ተቋም የሚተው ያለመሆንና በቅንጅት መሠረት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የግብረሀይሉ አባላት በሰጡት አስተያየት ኦዲት ባገኘባቸው ጉዳዮች እርምት አወሳሰድ ላይ ማትኮር እንደሚገባና እርምጀ መወሰድ ያለበት እየተወሰደ መሄድ እና መስተካከል ያለበትም በፋይናንስ አሰራር መታረም እንደሚያስፈልግ ለዚህም ሁሉም ሀላፊነት መውሰድ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

በተከተል ወ/ሚካኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *