የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና የህዝብ ግኑኝነት አመራሮች የገቢ አሰባሰቡ ውጤታማ እንዲኾን የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ገቢዎች ቢሮ፣በፍቃደኝነት ግብር የመክፈል ባህል እንዲዳብር ለማስቻል ያለመ የባለድርሻ አካላት ምክክር በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

የውስጥ ገቢ በአግባቡ በመሰብሰብ የክልሉ ህዝቦች ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ የአስተምህሮ ስራ ወሳኝ መኾኑን ነው የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ህይወት አሰግድ በመክፈቻ ንግግራቸው የገለጹት።

የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና የሚዲያ አመራሮች በክልሉ የገቢ አሰባሰብ ሥራው ውጤታማ እንዲኾን የበኩላቸውን እንዲወጡም ወ/ሮ ህይወት ጥሪ አቅርበዋል።

በሮው የክልሉን ህዝቦች የዘመናት ጥያቄ የኾነውን ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት ጥያቄ በየደረጃው ምላሽ እንዲያገኝ በገቢ አሰባሰብ የባለድርሻ አካላትን በባለቤትነት በማሳተፍ አበክሮ እየሰራ ይገኛልም ነው ያሉት ሃላፊዋ።

ግብር እና ታክስ በፈቃደኝነት የመክፈል ባህል ከግብር ከፋዩ የግንዛቤ ደረጃ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ እንደሆነ ያስረዱት ወ/ሮ ህይወት በአጠቃላይ በታክስ ህግ በቂ ግንዛቤ የጨበጠ ዜጋ የማንንም ግፊት ሳይጠብቅ ግዴታውን የመወጣት ዕድል ይኖረዋል ብለዋል።

ግብር ከፋዮች ግንዛቤ እያደገ ሲሄድ ታክስ በግዴታ የሚጣል ሽክም ሳይሆን የህልውና መሠረትና የዜግነት ክብር መገለጫ መኾኑን እየተረዱ እንደሚሄድም ነው ኃላፊዋ የገለጹት።

ቢሮው በበጀት ዓመቱ 18.4 ቢሊዮን ብር ገቢ በመሰብሰብ የክልሉ መንግሥት ወጪ 64.5 ከመቶ ለመሸፈን ዘርፍ ብዙ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝም ነው የጠቆሙት።

የቢሮ ምክትል ሃላፊና የትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፀደቀ ከፍታው እንደገለጹት፥ በገቢ አሰባሰብ ስርዓትና ህግ ማስከበር ላይ የሚዲያ አመራሮችና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ሚና ከፍተኛ ነው።

የገቢ አሰባሰብ ስራው ውጤታማ እንዲሆን የባለድርሻ አካላት ቁርጠኝነትና ትብብር እንደሚሻ ያስገነዘቡት አቶ ፀደቀ በመድረኩ የተገኙ የባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን በተገቢው እንዲወጡም ጠይቀዋል።

የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ግርማ ባሻ በበኩላቸው፥ የገቢ መሠረት በማስፋትና አሟጠው በመሰብሰብ ለክልሉ ልማት ማዋል እንደሚገባ በመጠቆም፣

የባለድርሻ አካላት በቂ ግንዛቤ በመያዝ በፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የገቢ አሰባሰብ ባህል እንዲዳብር የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

በመድረኩ በክልሉ የሚገኙ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች፣ የሚዲያና ህዝብ ግኑኝነት አመራሮች እንዲሁም ሌሎች የባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *