




በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የደን፣ አከባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ቢሮ በFOLUR ፕሮጀክት፣ በተመረጡ ሁለት ወረዳዎች ጥምር ግብርናን ለማስፋፋት ያለመ የባለድርሻ አካላት ውይይት በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።
ቀጣይነት ያለውን ጥምር የግብርና ስራዎችን በማስፋፋት የአምራቾችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚገባም ነው የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ለማ ገ/ሚካኤል የገለጹት።
በፕሮጀክቱ በተመረጡ ሁለት ወረዳዎች የጥምር ግብርናን ውጤታማ በሆነ መልኩ ተግባራዊ በማድረግ ወደ ሌሎች የክልሉ አከባቢዎች ማስፋፋት እንደሚገባም ነው አቶ ለማ የገለጹት።
ገበያ መር ጥምር ግብርና የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባሻገር ለሴቶችንና ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፈጠር የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንደሚያሳድግም ነው የፕሮጀክቱ አስተባባሪ በእውቀቱ ሀይሌ (ዶ/ር) ያስረዱት።
ለአየር ንብረት የማይበገር ዘላቂ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጥምር ግብርና የጎላ ፋይዳ እንዳለው የገለጹት ዶ/ር በእውቀቱ በተላይም በተመረጡ ወረዳዎች ለፍራፍሬ እርሻ ያለውን ምቹ አጋጣሚ በተገቢው በመጠቀም በክላስተር ማልማት ይገባል ብለዋል።
ጥምር ግብርና የደን መመናመንና የአፈር መታጠብን በመከላከል የገጠሩን ማህበረሰብ ችግር በዘላቂነት የሚቀርፍ እንደሆነ ያስረዱት አስተባባሪው ለተግባራዊነቱ የባለድርሻዎች ቅንጅት መጠናከር እንዳለበት አንስተዋል።
የካፋ ዞን ግብርና አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ መምሪያ ኃላፍ አቶ ገረመው ገብሬ በበኩላቸው በተመረጡ አከባቢዎች ለሚገኙ አርሶአደሮች ግንዛቤ በመፈጠር ወደ ተግባር መግባት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ጥራት ያላቸውን ዘር በመለየት ለአርሶአደሮች ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ ያስገነዘቡት አቶ ገረመው በሽታን ከመከላከል አኳያ ከዩኒቨርስቲዎችና ከምርምር ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራት ይገባል ብለዋል።
በክልሉ ካፋ ዞን፣ጊምቦ እና በቤንች ሸኮ ዞን፣ሼይ ቤንች ወረዳ በፕሮጀክቱ ድጋፍ የጥምር ግብርና ለማስፋፋት በኢትዮጵያ የደን ተቋም የተደረገው የዳሰሳ ጥናት ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።
በተመረጡ አከባቢዎች ያለው ስነ-ምህዳር ለአትክልት እርሻ አመቺ እንደሆነ የገለጹት የመድረኩ ተሳታፊዎች ወደ ተግባር ስገባ ማነቆ ልሆኑ በሚችሉ የዘር አቅርቦት፣ በሽታ መከላከል እንዲሁም የሰለጠነ የሰው ሀይል አቅርቦት ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል።
ለፕሮጀክቱ ዓላማ ስኬት የሚጠበቅባቸውን ለማበርከት ቁርጠኛ እንደሆነ ያስታወቁት ተሳታፊዎቹ ልምድና ተሞክሮዎቻቸውን በማጋራት እንዲሁም በዘር አቅርቦት እና የአቅም ግንባታ ስልጠና ድጋፍ ለመስጠትም ዝግጁ እንደሆኑ አስታውቀዋል።
ፕሮጀክቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዕቅድ በማዘጋጀት በተመረጡ ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ ቀበሌዎች የጥምር ግብርና ስራውን ተግባራዊ እንደሚያደርግም በውይይቱ ተገልጿል።
