






በቦንጋ ከተማ አስተዳደር ጊዜያዊ የሰንበት ገበያ ማዕከል ተጀመረ።
የሰንበት ገበያ የተለያዩ መሠረታዊ ዕቃዎች ላይ የሚታየውን የዋጋ ጭማሪ በማስተካከል ሸማቹ ማህበረተሰብ ተጠቃሚ እንድሆን ለማድረግ ታስቦ እንደሆነ የቦንጋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አስማማው አደመ ተናግረዋል።
የኑሮ ውድነትንና የዋጋ ንረት ለመቀነስ የሰንበት ገበያ አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት ከንቲባው ይህንን በዘላቂነት ለመተግበር እየተሰራ መሆኑንም ከንቲባው ገልጸዋል።
አሁን ላይ በገበያው የቀረቡት መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ሲሆኑ በቀጣይም እየታየ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ግንኙነት በማድረግ ሌሎች አስፈላጊ ምርቶችን የማቅረብ ስራ ይሰራልም ብለዋል።
አምራቾች ምርት አዘጋጅተው የገበያ ትስስር ያልተፈጠረው በቦንጋ ከተማ በሚደረገው ሰንበት ገበያ አምጥተው መሸጥ እንደሚችሉ እና ሸማቾችም በቅናሽ ዋና ገዝተው መጠቀም እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የካፋ ዞን ንግድና ኢንቨስትመንት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ገ/ስላሴ እንዳሉት ያለምንም ምክንያት ዋጋ ጭማሪ የሚደረግባቸው የፍጆታና የተለያዩ ዕቃዎች ዋጋ ለመቀነስና ኑሮ ለማረጋጋት በመንግሥት የተወሰደ መፍትሔ ሰንበት ገበያ ማቋቋም እንደሆነ ተናግረዋል።
ሰንበት ገበያ ከአምራቾች፣ከዩኒየኖችና ከማህበራት ምርቱን በቀጥታ ለሸማቹ ማህበረሰብ በበመጣጣኝ ዋጋ አቅርበው እንዲጠቀሙ ማድረግ እንደሆነ አስረድተዋል።
በዕለቱ የተጀመረው ጊዜያዊ የሰንበት ገበያ በሳምንት ሁለት ቀን የሚደረግ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ኃላፊው ይህንን ዘላቂ ለማስጀመር በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በቦንጋ ከተማ የተጀመረው የሰንበት ገበያ ውጤታማ እንደሚሆን ተናግረዉ ሌሎች ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ይህንን ተሞክሮ በመውሰድ ማስጀመር አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል።
የቦንጋ ከተማ ኢንዱስትሪና ንግድ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ወዳጆ ደሳለኝ በበኩላቸው የተጀመረውን የሰንበት ገበያ ማዕከል በቋሚነት ለማድረግ በከተማ አስተዳደር ሼድ ለመስራት ሙሉ ቅድሜ ዝግጅት መጠናቀቁን አስረድተዋል።
የሰንበት ገበያ ማስጀመሪያ መርሃ ግብርን የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደን ጨምሮ ሌሎች ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ጎብኝቷል ሲል የዘገበው የካፋ ዞን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው ።
