የዘንድሮው የማሽቃሮ በዓል በታላላቅ ሀገራዊና ታሪካዊ ክስተቶች ታጅቦ በድርብ ደስታ ይከበራል – አቶ ፍቅሬ አማን

Spread the love

የህዳሴው ግድብ ምርቃትና የካፋው ንጉስ የታቶ ጋኪ ሻሬቾ ዘውድ መመለስ ለበዓሉ ልዩ ድምቀት ሰጥተውታል ስሉ አቶ ፍቅሬ አማን ገልጸዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን፣ ለካፌቾ ብሔር የዘመን መለወጫ ‘ማሽቃሮ’ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ኃላፊው በመልዕክታቸው ፣ የዘንድሮው በዓል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በታላቅ ስኬት መመረቅና የካፋ ህዝብ የዘመናት ጥያቄ የነበረው የንጉስ ታቶ ጋኪ ሻሬቾ ዘውድ መመለስ ጋር ተዳምሮ በዓሉን ‘ድርብ ደስታ’ እንዳደረገው ገልጸዋል።

የማሽቃሮ በዓል፣ ጨለማው የክረምት ወቅት አልፎ ብሩህ ዘመን መግባቱን የሚያበስር፣ ተፈጥሮ የምታድስበትና አዲስ ተስፋ የሚሰነቅበት ታላቅ የባህልና እምነት መገለጫ መሆኑን አቶ ፍቅሬ ገልጸዋል። “በዓሉ ህዝቡ ላለፈው ዘመን ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት፣ ለመጪው ዘመንም ሰላምን፣ ጤናንና በረከትን የሚለምንበት የተቀደሰ ክዋኔ ነው” ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር ማሽቃሮ የይቅርታ፣ የእርቅ፣ የወንድማማችነትና የአንድነት እሴቶች የሚጎሉበት በመሆኑ ለሀገራች ሰላምና ለጠንካራ ማህበረሰብ ግንባታ ያለው ፋይዳ የላቀ ነው ሲሉ አክለዋል።

“የዘንድሮውን በዓል ልዩ የሚያደርገው የኢትዮጵያውያን የዘመናት ህልምና የቁጭት መልስ የሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ በስኬት መመረቁና የካፋ ህዝብ የረዥም ዓመታት ጥያቄ የነበረው የንጉስ ታቶ ጋኪ ሻሬቾ ዘውድ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ወደ ህዝቡ መመለሱ ነው” ያሉት አቶ ፍቅሬ፣ “እነዚህ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ለካፋ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያዊያን የደስታ ምንጭ ናቸው” በማለት “እንኳን ደስ አላችሁ፣ እንኳን ደስ አለን!” ብለዋል።

“እንደ ማሽቃሮ ያሉ ባህላዊ እሴቶቻችን የአብሮነታችን ማሰሪያና የአንድነታችን ምሰሶዎች ናቸው” ያሉት ኃላፊው፣ “እነዚህን እሴቶች በአግባቡ ስናስተዋውቃቸውና ስንንከባከባቸው፣ የቱሪዝም መስህብ በመሆን ለሀገራችን የብልጽግና ጉዞ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ” ሲሉ አስገንዝበዋል።

መንግስት የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶቻችን ተገቢውን ክብርና ጥበቃ እንዲያገኙ በማድረግ ለቀጣዩ ትውልድ ለማሻገር በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ ለመላው የካፊቾ ብሔር አባላት በድጋሚ “እንኳን ለብርሃናማው የማሽቃሮ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!” ሲሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *