ክልል አቀፍ የተቀናጀ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት በይፋ ተጀመረ

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ክልል አቀፍ የተቀናጀ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ በዳውሮ ዞን ታርጫ ጤና ጣቢያ በይፋ ተጀመሯል።

ከግንቦት 6/2017 እስከ ግንቦት 15/2017 በሚቆየው በዚሁ የክትባት ዘመቻ በክልሉ ዕድሜአቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ 527 ሺህ 954 ህጻናት የክትባት አገለግሎት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ታውቋል።

በማስጀመሪያ መርሃግብር የተገኙ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ የጤናና ጤና ነክ ግብአት ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣና ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አሰፋ ዘመቻው ስኬታማ እንዲሆን የህብረተሰብ የነቃ ተሳትፎና የጤና ባለሙያዎች ቁርጠኛነት ወሳኝ እንደሆነ አንስተዋል።

በዘመቻው ከኩፍኝ መከላከያ ክትባት በተጨማሪ ሌሎች የክትባት፣ የህክምናና የልየታ ስራዎች በቅንጅት እንደሚሰራ አቶ ሙሉቀን አስረድተዋል።

የዳውሮ ዞን ጤና መምሪያ ሀላፊ አቶ አስራት ቸርነት በበኩላቸው ህፃናትን በአግባቡ በማስከተብ በክትባት መከላከል የሚቻሉ በሽታዎችን መከላከል እንደሚገባ ገልጸዋል።

ጤናው የተጠበቀ ትውልድ ለሀገር ብልፅግና ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመረዳት ህብረተሰቡ ህፃናትን በንቃት ማስከተብ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በዳውሮ 111 ሺ በላይ የሆኑ እድሜአቸው ከአምስት አመት በታች የሆኑ ህፃናት የክትባት አገለግሎት ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ታውቋል።

በዝግጅት ምዕራፍ የታዩ መልካም አፈፃፀሞች በተግባር ምዕራፍ ልደገም ይገባል ያሉት አቶ ሙሉቀን አሰፋ የክልሉ ጤና ቢሮ ለዘመቻው ስኬታማነት የሚያደርገውን ድጋፍና ክትትል አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የክትባት ዘመቻው ከዛሬ ግንቦት 6/2017 ጀምሮ እስከ ግንቦት 15/2017 ድረስ በክልሉ በሁሉም አከባቢዎች እንደሚሰጥ ተነግሯል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *