




በክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ አዘጋጅነት የሚካሄደው ክልላዊ የሀብት ጥናት በተጨባጭ የክልሉን ሀብቶች እና ጸጋዎችን መለየትና ጥቅም ላይ ለማዋል ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ተብሏል።
የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ቤተልሄም ዳንኤል መድረኩን በንግግር ሲከፍቱ እንደተናገሩት ቢሮው በአዋጅ ከተሰጡት ተግባሮች አንዱ የክልሉን ሀብቶች እና ጸጋዎች በማጥናት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ክልል በግብርና ፣ በኢንዱስትሪ ፣ በማዕድንና መሰል ሀብቶችን በተጨባጭ በማጥናትና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸውን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ በመለየት ለጥቅም ማዋል ይገባል ብለዋል።
ክልሉ ከተቋቋመ ወዲህ የመጀመሪያውና ታሪካዊ ጥናት ይሆናል ያሉት ኃላፊዋ ተግባሩ ውጤታማ እንዲሆንም በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ፣ በጥናትና ምርምር ስራዎች ላይ ቆይታ ያላቸው ምሁራንን ያካተተ የአጥኚ ቡድን መመረጡን ገልጸዋል።
ጥናቱ በራሱ የሚወስደው ጊዜ ፣ ልፋትና ድካምን ታሳቢ እናደርጋለን ያሉት ወይዘሮ ቤተልሄም ይሁን እንጂ የመረጃው ተአማኒነት እና ትክክለኛ የክልሉን ሀብቶች ለይቶ ከማጥናት አንጻር በትኩረት እንዲሰራም ጠይቀዋል።
መድረኩም በዋናነት የአጥኚ ቡድን አባላትን የማገናኘት ፣ የማስተዋወቅ እንዲሁም ወደ ጥናት ስራው ለመግባት የቅድመ ዝግጅት ስራዎችና ክልላዊ ሀብቶች ላይ መነሻ ውይይት ለማድረግ ታስቦ መሆኑን ጠቁመዋል። በመድረኩ ከሚዛን ቴፒና ቦንጋ ዩኒቨርስቲ የዘርፉ ምሁራን ፣ ከስታትስቲክስ ቢሮ እንዲሁም ከክልሉ የተለያዩ ተቋማት ለጥናቱ የተመረጡ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
በክላዊ የሀብት ጥናት ማስጀመሪያ መድረክ ረዳት ፕሮፌሰር ጥምቀቴ አለሜና ዶክተር አንዱአለም በጋሻው የጥናቱን ማስጀመሪያ ሰነድ እያቀረቡ ይገኛሉ።
