በአንድራቻ ወረዳ በተለያዩ የግብርና ልማት ስራዎች የተሰማሩ አርሶአደሮች ውጤታማ መሆናቸውን ተናገሩ

Spread the love

በአንድራቻ ወረዳ ጨገቻ ቀበሌ ጉምቢ ካቻ መንደር ከሌማት ትሩፋት ተግባራት አንዱ የሆነው የማር መንደር ምልከታ ተደርጓል።

በቀበሌው ትኩረት ከተሰጠባቸው የሌማት ትሩፋት ተግባራት አንዱ የማር መንደር ሲሆን ይህም ውጤታማነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን አርሶአደሮች ተናግረዋል።

የሸካ ዞን ግብርና አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ መምሪያ ምክትል ኃላፊና የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አረጋኸኝ አለሙ በመስክ ምልከታው ወቅት እንደገለጹት ሀገራዊ የሌማት ትሩፋት መርሃግብርን ተከትሎ በዞኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረው የበጋ መስኖ ስንዴን ጨምሮ በሌማት ትሩፋት ስራዎች የማር መንደር፣የቀይ ስጋ መንደር፣የወተት መንደር ፣የዶሮ መንደር በየቀበሌያት ተለይተው በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

አቶ አረጋኸኝ አክለውም ዞኑ ለማር ምርት ምቹ ስነምህዳር ያለው አካባቢ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እምቅ የማር ምርት የሚመረትበት መሆኑን ገልጸው ዞኑ በየዓመቱ ከ35 ሺህ ቶን በላይ የማር ምርት ለማዕከላዊ ገበያ የሚያቀርብ መሆኑን ተናግረዋል።

ጨገቻ ቀበሌ ጉምቢ ካቻ የማር መንደር ከ20 በላይ ንብ አናቢዎች በኩታ ገጠም ተሰማርተው ውጤታማ ከሆኑት መካከል አቶ ወርቁ ዳሾ አንዱ ሲሆኑ በምርቱ ከራሳቸው ባለፈ ልጆቻቸውን ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በመላክ ማስተማር ላይ መሆናቸውን ተናግረው የገቢ አቅማቸውም በዚያ ልክ ማደጉን ጠቁመዋል።

ከአንድ ዘመናዊ የማር ቀፎ እስከ 35ኪሎ ግራም የሚጠጋ የማር ምርት በማግኘት ላይ መሆናቸውን ተናግረው በአሁኑ ሰአት ከ18 በላይ ከሚሆኑ የንብ ቀፎዎች ማር እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በቀበሌው በዘመናዊ የንብ ማነብ ስራ ላይ ተሰማርተው ውጤታማ ከሆኑ አርሶአደሮች መካከል ያነጋገርናቸው ሌላው አቶ አለሙ ኃይሌ አንዱ ሲሆኑ ቀደም ሲል ባህላዊ አሰራርን ተከትለው ከሚያገኙት ይልቅ አሁን ተጠቃሚነታቸው መጨመሩን የሸካ ዞን ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመለክታል።

እንደ አርሶአደሩ ገለፃ በአንድ የማር ምርት ወቅት እስከ 4 መቶ ኪሎ ግራም የማር ምርት በማግኘት ላይ መሆናቸውን ተናግረው የገቢ አቅማቸውም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መሆኑን ገልፀዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *