




እየተካሄደ በሚገኘው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባኤ፣ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ምላሽ ሰጥተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንደገለጹት÷ በክልሉ የኅብረተሰብ የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ሰፊ ትኩረት ተሰጥተው እየተሰራ መኾኑን በማንሳት በዚህም ከጊዜ ወደ ጊዜ የኅብረተሰብ እርካታ ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።
በክልሉ በሚከናወኑ የልማት ሥራዎች የላቀ የኅብረተሰብ ተሳትፎ እየታየ እንደኾነ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ በቀጣይም የኅብረተሰብ ተሳትፎ እየተጠናከረ መሄድ እንዳለበት አሳስበዋል።
በክልሉ ከተሞች የአግልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል መጠነ-ሰፊ ተግባራት መከናወኑን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ በዚህም የመሬት ምዝገባ፣ የካዳስተር እና የዲጂታል አግልግሎት በመዘርጋት የአግልግሎት አሰጣጥ ማሻሻል እየተቻለ ነው ብለዋል።
በክልሉ እየተሰሩ ያሉ የፌዴራል መንገዶች አፈጻጸም በመገምገም ችግሮችን በመለየት የመፍታት ሥራው ከባለድርሻዎች ጋር እየተሰራ መኾኑን ያነሱት ዶ/ር ነጋሽ÷ ግንባታው በተቀመጠው ጊዜ እንዲሳለጥ የኅብረተሰብ ትብብር ማጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የጤና ተቋማትን ደረጃ በማሻሻል የሚሰጡ አግልግሎት ፍትሀዊ ተደራሽነት ለማረጋገጥ የክልሉ መንግስት የህንጻ ግንባታ፣ የቁሳቁስ ማሟላት፣ የታዳሽ ሀይል አቅርቦት እንዲሁም የሰው ሀይል የማሟላት ሥራ በባለድርሻ አካላት ቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ ነው ዶ/ር ነጋሽ የገለጹት።
ርዕሰ መስተዳድሩ÷ የክልሉ ምክር ቤት በቋሚ ኮሚቴዎች በኩል የታችኛው ምክር ቤት ለማጠናከር እንዲሁም የአስፈጻሚ ተቋማት ተግባራት ላይ የጀመረው ውጤታማ እንቅስቃሴ አበረታች መኾኑን በመጥቀስ በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
ከተሞች ለኑሮ ምቹ እንዲሁም የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንዲኾኑ የተጀማመሩ የከተማ ልማት ሥራዎች መጠናከር እንደሚገባ ነው ርዕሰ መስተዳድሩ ያሳሰቡት።
የክልሉ መንግሥት ከኅብረተሰቡ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች አቅም በፈቀደው ሁሉ ለመፍታት ቁርጠኛ መኾኑን በመግለጽ በዚህም ሄደት የኅብረተሰብ ተሳትፎ መጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
