



“ከመልካም አመራርነት ወደ ታላቅ አመራርነት መሻገር ” በሚል መርህ ቃል ለክልሉ አመራሮች በተዘጋጀው የአቅም ግንባታ ስልጠና የክልሉ አጠቃላይ አመራር እንዲሁም የዞን፣ የወረዳ እና የከተማ አስተዳደር አስተባባሪዎች ተሳትፈዋል።
ስልጠናው በአመራሩ ዘንድ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነትን በመፈጠር፤ አመራሩ በእያንዳንዱ ተግባር ላይ ፍጥነትና ፈጠራ በማከል ለክልሉ ሁለንተናዊ ለውጥ አስተዋጽኦ እንዲያበርክት የሚያዘጋጅ መኾኑን ነው ተሳታፊዎች የገለጹት።
አመራሩ በስልጠናው ያገኘውን የጽንስ ሀሳብ ዕውቀት በተጨባጭ ወደ ተግባር በመቀየር የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መትጋት እንደሚገባ ነው ተሳታፊዎች የገለጹት።
ክልሉ ብዝሀ ማንነትን በውስጡ ያቀፈ በመኾኑ እውነተኛ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት እንዲሁም ኅብረ-ብሄራዊ አንድነት በማጎልበት ለሀገራዊ ትልም መሳካት አስተዋጽኦ የሚያበረክት የበቃና የነቃ አመራር ለመፈጠር መድረኩ የጎላ ፋይዳ እንዳለውም ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የጠቆሙት።
አመራሩ አሁን ያለው ዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ ነባራዊ እውነታዎችን በተገቢው በመረዳት ራሱን ከተለዋዋጭ ሁኔታዎች ጋር መለወጥ እንዳለበትና የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተለያዩ ስልቶችን እንዲቀይስ ግንዛቤ የፈጠረ እንደነበረም ተናግረዋል።
የህዝብ የልማት ጥያቄዎችን በተገቢው ለመመለስ በአመራር እና በህዝብ መካከል ጠንካራ መተማመን መፈጠር አስፈላጊ መኾኑንም በስልጠናው ሰፊ ልምዶች የተጋራበት መኾኑን ነው የገለጹት።
አመራሩ በየጊዜው የሚገጥሙ ጥቃቅን ጊዜያዊ ፈተናዎች ትልቁን እይታችንን እንዳይጋርዱ ነገሮችን አሻግረው ማየትና ለችግሮቹም አማራጭ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያበጅ ስልጠናው አለምአቀፍ ተሞክሮዎችን በማጋራት ጭምር ትምህርት የሰጠ መኾኑን ነው ተሳታፊዎቹ የገለጹት።
በክልሉ ያለውን ውስጣዊ አቅሞችን በአግባቡ በመጠቀም ሀብት ፈጥሮ የዜጎችን ኑሮ በዘላቂነት ለማሻሻል እንዲሁም በቀጣይ ሀገራዊ ተልዕኮዎችን በላቀ ተነሳሽነት ለመወጣት ተነሳሽነትን የፈጠረ ስልጠና እንደነበረም ተናግረዋል።
በየጊዜው የሚሰጡ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች አመራሩ የህብረተሰቡን ችግር ተረድተው የአስተሳሰብና የተግባር አንድነትን በመፍጠርና ለጋራ ዉጤት እንዲዘጋጅ የሚያስችል መኾኑንም ነው የገለጹት።
በየደረጃው የበቃና የነቃ አመራር ለመፈጠር
ተከታታይነት ያለው ስልጠና በቀጣይም በትኩረት መስጠት እንዳለበትም ነው ተሳታፊዎች የገለጹት።
በአጠቃላይ ስልጠናው በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚነሱ የልማት ጥያቄዎችን በላቀ ዝግጁነት ለመመለስ ከግል ስብዕና ግንባታ ጀምረው የአመራርነት ብቃት ለማሳደግ የሚያስችል መኾኑን ጨምረው ተናግረዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
