የአካባቢና የሀገር አንድነት የሚረጋገጥበት የካፈቾ ብሔር ዘመን መለወጫ “ማሽቃሮ” በዓል

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከሚገኙ ከ6ቱ ዞኖች አንዱ የሆነው የካፋ ዞን በርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ የሚኖሩበት ዞን ነው፡፡ ከነዚህም መካከል ነባር የሆኑ ካፈቾ፣ ናኦና ጻራ ይጠቀሳሉ፡፡

ብሄረሰቦቹ የራሳቸው ባህል፣ ታሪክ፣ እሴት እና ቋንቋ ያላቸው ናቸው፡፡ የራሳቸው የሆነ የበዓል አከባበር ስርዓትም አላቸው፡፡ ከነዚህም ውስጥ የካፈቾ ብሔር አንዱ ሲሆን የራሱን የሆነ በርካታ ባህል፣ታሪክ ወግ፣ ቅርስ፣ እሴትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ነው፡፡

ከማይዳሰሱ የካፈቾዎች ባህልና ቅርሶች መካከል የብሔሩ የዘመን መለወጫ በዓል ዋነኛው ነው፡፡ ለዚህም በርካታ ታሪኮች በፁሁፍ እንደሚገልጹት የካፈቾ ብሔር የራሱን ዘመን መለወጫ በዓል የአዝመራ ወቅት ማብቂያ ወራትን ተከትሎ በስፋት ይከበራል፡፡

እንደ አውሮፒያዉኖች አቆጣጠር ከ1887 እሰከ 1983 ድረስ የካፈቾ ብሔር ይሁን ሌሎች ብሔረሰቦች የራሳቸው ባህልና ታሪክ ያላቸው በመሆኑ የጨለማ ዘመናትን ያሳለፋቸውን ፈጣሪ የሚያመሰግኑበት ወቅትም አሏቸው፡፡

የካፈቾ ብሔር ዘመን መለወጫ /ማሽቃሮ በዓል የአዝመራ አቆጣጠር መነሻ አድርጎ የሚከበር የዘመን መለወጫ በዓል ነው፡፡ ዛሬም ድረስ የአርሶ አደሮች የአዝመራ አቆጣጠር ከሐምሌ 1ጀምሮ ያለውን 77ተኛ ይሉታል፡፡ ይህም የአዝመራ መጀመሪያ እንደማለት ነው፡፡

በዚህም 77ተኛ ቀን ወደኋላ በመቁጠር መስከረም 13 ሁልጊዜ የካፈቾ ዘመን መለወጫ በዓል ይከበረል፡፡ የአዝመራ አቆጣጠር የቆይታ ጊዜያቸውም 77ኛ እስከ 35ኛ በመባል ይታወቃል። በዓሉ የአዝመራ የእህል ዘሮችን ዘርቶ በማጠናቀቅ በመጨረሻ የአዝመራ ማብቂያ ተብሎ የሚከበር በዓል ነው፡፡

የበዓሉ አከባበር በየደረጃው በህዝቡ ዘንድ እየተከበረ የሚመጣ ሲሆን በቦንጌ ሻምበቶ በንጉሥ መንደር በየዓመቱ በመስከረም 13 ቀን ይከበራል፡፡

በዓሉ ቀደምት የካፈቾዎች ታሪካዊና ባህላዊ ይዘት ያለው የነገስታት በዓል በመሆኑ ከየትኛውም እምነት ጋር ፈጽሞ አይገናኝም፡፡የሁሉም እምነት ተከታዮች ያለ ምንም ልዩነት የሚያከብሩት የህዝብ በዓል ሆኖም ቆይቷል፡፡ የበዓሉ ቅድመ ዝግጅት መጨረሻ 300 ፈረሶች፣ 100 ቀይ ልብሶች ፣ 100 ነጭ ልብሶችና 100 ዳለቻ ልብሶችን በማልበስ ማልደው ወደ ሾሻ ሞጎ የነገስታት መቃብር ጠሎ ወረዳ ይሄዳሉ፡፡

ነገስታት በፈረሶቻቸው ጦርና ጋሻ ይዘው ሾሻ ሞጎ የሚሄዱበት ምክንያት የአከባቢውን ደህንነት ለማረጋገጥና ለነገስታት መቃብር ያላቸውን አክብሮት ለማመላከት ነው፡፡

በዚሁ ቀን የንጉሥ አካባቢ በጥብቅ ይጠበቃል ሁከትና ብጥብጥ አይኖርም እንቅስቃሴ አይፈቅድም ይሄ የሚሆነው ደግሞ ለንጉሡ ደህንነት ነው፡፡

ሌላው

ሃውቶ የሚባል በበጋ ሆነ በክረምት የማይደርቅ ሃረግ በረዥሙ ታስሮ ሁሉም የበዓሉ ታዳሚዎች ሃረጉን መያዝ የምችሉ በመያዝ፣ መያዝ የማይችሉ ሃረጉን የያዙትን ሰዎች ልብስ በመያዝ ለቀጣይ ዓመት ፈጣሪ በሰላም እንዲያደርሳቸው በአንድነት መርቀው በሬው ይታረዳል፡፡

ከተበላ በኋላ በአራት አቅጣጫዎች ጎኖ ይወቀራል፡፡ እነዚህም አቅጣጫዎች ከያ-ኬላ፣ ሻራ፣ ሻፓ እና አንድራቻ ኬላዎች የተቀመጡ ጎኖዎች ይወቀሩና ታችኛው የህብረተሰብ ክፍሎች በዓሉን እንድያከብሩ መልዕክት ይተላለፋል፡፡

የበዓሉ ቆይታ በንጉሥ አካባቢ እስከ አንድ ወር ድረስ በጨዋታና በዘፈን የሚቆይ መሆኑን የተጻፉ መረጃዎች እና ታላላቅ የብሔሩ አባቶች ያስረዳሉ ፡፡

የካፈቾ ብሔር የአዝመራ ማብቂያ ዘመን መለወጫ /ማሽቃሮ በዓል ለሀገር አንድነትና ለማህበራዊ ማስተጋብር ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ በዞኑ የሚገኙት ብሔር ብሔረሰቦች ያለ ምንም ልዩነት በዓሉን በጋራ ያከብራሉ፡፡ የእምነት እና የሀይማኖት ልዩነት ቢኖርም ሁሉም የየእምነቱ ተከታዮች በጋራ ያከብራሉ፡፡

በዓሉ የተጣላውን በማስታረቅ፣ የተራራቁትን በማቀራረብ የአካባቢና የሀገር አንድነት የሚረጋገጥበት በዓል ነው፡፡ ሁሉም ሰው በእኩል የሚስተናገዱት ሆኖ ከሌሎች በዓላት ይለያል፡፡

በዓሉ የህዝብና የሀገር በዓል በመሆኑ ለአዲስ ዓመት ዕቅድ ቀርቦ በጋራ አቅጣጫ የሚያዝበት በዓል ነው፡፡ ከበዓሉ ከአንድ ሳምንት አስቀድሞ ወራፈራሻና ምክረቾ ተጠርቶ ሥራዎች ይገመገማሉ፡፡

ግምገማው በጉጀራሻ ተከታይነት ከተማራሻና አወራሻ አስተባባሪነት የሚመራ ሆኖ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በዝርዝር ይገመገማል፡፡ በተለይም የንግድ እንቅስቃሴ፣ የግብር አሰባሰብ ሁኔታ፣ ጸጥታ እና ተመሳሳይ ጉዳዮች በተጨማሪ የተሿሚዎች ስነምግባር ትኩረት ተሰጥቶ የምገመገምበት ነው፡፡

ግምገማው ከአንድ ወራፎ ጋር ተወዳድሮ ጥሩ ውጤት ያመጣ ሹመት የሚሰጥበት እና ደካማ ዉጤት ያመጣውን ከሹመት በማውረድ በእነሱ ምትክለተተኪዎች ሹመትይሰጣል፡፡ ጀግና የጦር ሽልማት ይሰጣል፡፡ የተገመገሙ ወይንም የታገዱት እንደየቅጣታቸው ታይቶ ለአደራሻ ቀርቦ ምህረት ይጠየቃል፡፡

በተከተል ወ/ሚካኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *