የማሽቃሮን ዕሴት በማዳበር ለልማትና ለህብረ ብሄራዊ አንድነት ግንባታ ማዋል ይገባል – ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)

Spread the love

የካፈቾ ብሔር የዘመን መለወጫ (ማሽቃሮ) ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሀላፊዎች፣ የባህል መሪዎች እና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት የነገስታት መናገሻ በኾነውና ከቦንጋ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው “ቦንጌ ሻምበቶ” ተከብሯል።

በክብረ በዓሉ ተገኝተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) የማሽቃሮ ዕሴት የኾኑ አብሮነትና አንድነትን በማጠናከር ለልማትና ለኅብረ ብሄራዊ አንድነት ግንባታ ማዋል ይገባል ብለዋል።

የዘንድሮው የማሽቃሮ በዓል የጥንት የካፈቾ ብሔር የስልጣኔና ታሪክ እንዲሁም ባህል መገለጫ የኾኑና ከ128 ዓመታት በፊት ከአከባቢው ተወሰደው የነበሩ የንግሥና ዘውድ እና ዙፋን ለባለቤቱ ህዝብ ለእይታ ክፍት በኾነበት በመኾኑ ልዩ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ የዘመናት ቁጭት የኾነውን በራስ ሀብት የመጠቀም መብት በህዝቦቿ ጥረት ባረጋገጥችበት ማግስት የሚከበር በመኾኑ የዘንድሮው ማሽቃሮ ታሪካዊ እንደሚያደርግ ነዉ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፣

በቀጣይም ይህንን አንድነት እና መተባበር በማጠናከር በሌሎች የልማት መስኮች ላይ መድገም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የካፈቾ ብሔር ድንቅ የተፈጥሮ ጥበቃ ባህል ባለቤት መኾኑን ያወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ የብሄረሰቡ ድልብ የእውቀትና ጥበብ መገለጫ የኾነውን ማሽቃሮ በመጠበቅ እና በማልማት ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚያስፈልግም በአጽንኦት ተናግረዋል።

ማሽቃሮ የአብሮነት፣ የአንድነት እና የእርቅ መገለጫ መኾኑን የገለጹት የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ በዓሉ በብሄረሰቡ ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ የአዲስ ዘመን ብስራት ነው ብለዋል።

ማሽቃሮ ካለው ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አኳያ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ እንደሚዘገበ የዞኑ መንግሥት እንቅስቃሴ መጀመሩን የገለጹት አቶ እንዳሻው የባለድርሻዎች ትብብር እንዲጠናከርም ጠይቀዋል።

የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፀጋዬ ማሞ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ማሽቃሮ የህዝብ ለህዝብ ትስስር በማጠናከር ለክልላዊ ለሀገራዊ አንድነት የጎላ ፋይዳ አለው ብለዋል።

ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ማሽቃሮን ጨምሮ ሌሎች በክልሉ የሚከበሩ በዓላትን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን አቶ ፀጋዬ ገልጸዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *