




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ገነት መኩሪያ በ2017 የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ”በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ! በሚል መሪ ቃል! በ14 የትኩረት መስኮች ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ተግባራት እስከአሁን ድረስ በተቀመጠው የስምሪት መስኮች ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ በተገቢው እየተሰራ እንደሚገኝና በየደረጃው የሚገኙ አካላት የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ መሆኑን ነው ወ/ሮ ገነት የገለጹት፡፡
የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አረንጓዴ አሻራ፣ የአቅመ ደካሞች ቤት ግንባታና እደሳ፣ ማዕድ ማጋራት፣ ደም ልገሳ፣ የተማሪዎች ማጠናከሪያ ትምህር፣ የትምህርትና ጤና ተቋማት መጠገን፣ መሰረተ ልማት ማጠናከር እና ሌሎችንም ማህበረሰብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
በዚሁ በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት 1ሚሊየን 187 ሺህ 145 በጎ ፈቃደኞችንና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ እስከአሁን 766 ቤቶችን የመገንባትና የማደስ ስራዎች መሰራታቸውን ያመላከቱት የቢሮ ኃላፊዋ ከዚህ ውስጥ 644,862 ወጣቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም በበጎ ፈቃድ የተሰማሩ ዜጎች ጉልበት በገንዘብ ሲተመን 877 ሚሊዮን 187 ሺህ 635 ብር የሚገመት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎች በማከናወን 2 ሚሊየን 233 ሺህ 864 የማህበረሰብ ክፍሎችን እስከአሁን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
በክልሉ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራ በህብረተሰቡ ውስጥ የመረዳደት ባህል ወደመሆን የተቀየረ መምጣቱን የጠቀሱት ወ/ሮ ገነት በዚህም ወጣት በበጎ ፈቃደኞች በማህበር በመደራጃት ህጋዊ እውቅና በማግኘት ተከታታይነት ያለው የሰበአዊ ድጋፍ የመስጠት እና የአብሮነት ተምሳሌት ወደ መሆንና ይህ ልምድ ወደ ህብረተሰቡ እየተሸጋገረ ነው ያሉት፡፡
ለበበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ ቀጣይነት ሁሉም የክልሉ ህዝብ ከበጎ ፈቃደኛ ጎን በመቆም በበጎ ፈቃድ በመሳተፍ፣ ለበጎ ፍቃደኝነት ወደ አካባቢ የሚመጡ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን የመቀበል ፣የመስተናድና አብሮ የመስራት ባህል ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ገልፀዋል፡፡
በክልሉ ባሉት አካባቢዎች ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ማህበረሰብን በጉልበት ፣በእውቀት እና በገንዘብ ድጋፍ በማድረግ የአእምሮ እረፍት የሚሰጥ ስራ አካል እንዲሆኑና በጎ ፈቃድ የህብረተሰባችን ባህል እንዲሆን የድርሻችውን እንዲወጡም ኃላፊዋ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
በተከተል ወ/ሚካኤል
