





የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ጤና ቢሮ የጤናና ጤና ነክ አገልግሎት ግብዓት ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን የዓመቱን ዕቅድ አፈጻጸም በታርጫ ከተማ እየገመገመ ነው።
በክልሉ ተርጫ ከተማ እየተካሄደ ባለው የዕቅድ አፈጻጸም ላይ በጤና ቢሮ የጤናና ጤና ነክ አገልግሎት ግብዓት ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አሰፋ እንደገለጹት በ2016 በጀት ዓመት በክልሉ የሚገኙ ነዋሪዎችን ጤና ለማስጠበቅ የጋራ ርብርብ ሲደረግ ቆይቷል።
ከዚህ የተነሣ በአገር ደረጃ ክልሉ በተሻለ ደረጃ ላይ መገኘቱን ገልጸው በቀጣይ እንደ አገር ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እንዲቻል ጤናው የተጠበቀ ማኅበረሰብ መፍጠር ወሳኝ መሆኑ ታምኖበት በትኩረት ተግባሩ እየተመራ መሆኑንም አስረድተዋል።
አልፎ አልፎ ከመድኃኒትና ከሕክምና ቁሳቁስ ስርጭትና ቁጥጥር አጠቃቀም እንዲሁም ጥራታቸው ያልተረጋገጠባቸውና የጥራት ጉድለት ያለባቸውን መድኃኒቶችን በመለየት ረገድ የሚታየውን ውስንነት ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ እንዳለም ገልጸዋል።
በውይይት መድረክ የተገኙ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ አቶ ወንድሙ ኩርታ በመክፈቻ ንግግራቸው የጤና ተቋማት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በተገቢው በመወጣት ለማኅበረሰቡ ተጠቃሚነት በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልጋቸውም ተናግረዋል።
በክልሉ ሁሉም የጤና ተቋማት ውስጥ የግብዓት ቁጥጥርና ስርጭት ላይ በተግባሩ አቅም መዳከም እንዳያጋጥም ለማስቻል በትኩረት ሊሠራ ይገባልም ብለዋል።
በውይይቱ የሁሉም ዞኖች የጤናና ጤና ነክ አገልግሎት ግብዓት ጥራት ቁጥጥር ዳይሬክተሮች የዓመታት ዕቅድ ሪፖርት ቀርቦ የሚገመገም ይሆናል።
በመቀጠልም የጤና አገልግሎት አስተዳደር ደንብ ቁጥር 017/2016ና የምግብ፣ መድኃኒት እና ትምባሆ ቁጥጥር ደንብ 018/2016 እንዲሁም የጤና ባለሙያዎች ፈቃድን በበይነ መረብ ማስጀመሪያ መርሃግብር ላይ ማብራሪያና ገለጻ እንደሚደረግ ከወጣው መርሃግብር ለመረዳት ተችሏል።
በውይይቱ የክልሉ ዋና አፈ ጉባዔ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት፣ ከየዞኖች የጤና አመራሮችና ባለሙያዎች፣ የግል ጤና ጤና ተቋማት ተወካዮች፣ ዳኞች፣ የፍትሕና የሚዲያ ባለሙያዎች ተሳታፊ ናቸው።
