የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በጭዳ ከተማ የአቅሜ ደካማ መኖሪያ ቤት ግንባታ አስጀመረ

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በኮንታ ዞን በምትገኘው ጭዳ ከተማ፣ አቅመ ደካማና ጠያቂ ለሌላቸው እናት የመኖሪያ ቤት ግንባታ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጀመረ።

ይህ የክረምት ወራት የበጎ አድራጎት ሥራ የክልሉ መንግሥት አቅመ ደካሞችን ለመደገፍ የያዘው ሰፊ መርኃ ግብር አካል መሆኑ ተገልጿል።

የቤቱ ግንባታ የተጀመረላቸው ወ/ሮ በየነች መኮንን፣ በከተማው ውስጥ በችግርና ያለረዳት በደሳሳ ጎጆ ውስጥ ይኖሩ ነበር። ወ/ሮ በየነች፣ መንግሥት እንደ እሳቸው ያሉ ረዳት የሌላቸውን ዜጎች መድረሱ ትልቅ ደስታ እንደፈጠረላቸው ገልጸው፣ ለተደረገላቸው ድጋፍ ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የጭዳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዓለሙ ኮቾ በበኩላቸው፣ አቅመ ደካሞችንና አረጋውያንን መደገፍ የብልጽግና ፓርቲ መንግሥት አንዱ መገለጫ መሆኑን ጠቅሰው፣ “ተግባሩ ለህሊና እርካታን የሚሰጥና በፈጣሪ ዘንድም በረከት የሚያስገኝ ነው” ብለዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ በረከት ኢዮብ፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜጎችን ማኅበራዊ ችግሮች በመፍታት ረገድ የብልጽግና ፓርቲ ካስቀመጣቸው ቁልፍ መርኃ ግብሮች አንዱ መሆኑን አስረድተዋል። “ፓርቲው ሰው ተኮር በመሆኑ መሠረታዊ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ችግሮች እየለየ መፍትሔ እየሰጠ ይገኛል” ሲሉ አክለዋል።

የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ፣ ግንባታው በፍጥነትና በጥራት አጠናቆ እንደሚያስረክብ ወ/ሮ በረከት አረጋግጠዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *