
ኢትዮጵያ አሁን ላይ ለ400 ሺህ ኤርትራውያን ስደተኞች መኖሪያ እና መጠለያ ቤት እንደሆነች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ሀገራችን ኤርትራውያኑን ጨምሮ ከተለያዩ ሀገራት የተሰደዱ በአጠቃላይ ለ1.3 ሚሊዮን ስደተኞች ቤት መሆን የቻለች ሀገር ናት ብለዋል።
ሀገራችንን በወጉ መገንባት ከቻልን ለዜጎቻችን ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም አርአያ መሆን የሚችል እና የሚተርፍ ውጤት ማምጣት እንደምንችልም አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በሕዝብ ቁጥር ሁለተኛ፣ ከዓለም ደግሞ 10ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ጠቅሰው፣ ይህ ሰፊ የሕዝብ ቁጥር እና ሰፊ የቆዳ ስፋት በትክክለኛ ዕቅድ እና ጥረት ከተመራ ለትልቅ ለውጥ መነሻ እንደሚሆንም አብራርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘው እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የተፈጥሮ ሀብት እና አስደማሚ የፈጠራ አስተሳሰቦች በጥቂት ጥረት ቢታገዙ ትልቅ ብሔራዊ ለውጥ ማምጣት ይቻላል።
ለወደፊት በራዕይ ቀጣዮቹን 10 እና 15 ዓመታት ታሳቢ ያደረገ የትብብር ሥራ ከተሠራ፣ ኢትዮጵያን ለብዙዎች ብርቅ፣ ለበርካቶች ደግሞ አስተማማኝ መጠለያና መሸሸጊያ ማድረግ ይቻላል።
ኢትዮጵያ ከዓለም ተቀባይ ብቻ ሳትሆን፣ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የራሷን የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችል ብቃት እና አቅም ያላት ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።
ለዜጎቿ የምትመች እና ለጎረቤቶቿ የምትተርፍ ኢትዮጵያን ለመገንባት በጋራ እና በትብብር መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ በስደተኞች አያያዝ አርዓያነት ያለው እና የሚደነቅ ተግባር እያከናወነች መሆኑን በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን በተለያዩ ጊዜያት መስክሯል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።
