የትምህርት ሥራዎች በሚዲያ እንዲተዋወቁ ለማስቻል እየተከናወነ ባለው ተግባር ውጤት እየተመዘገበ መጥቷል፦ አቶ የሺዋስ ዓለሙ

Spread the love

የክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር “ሳቢ ይዘት፣ ሙያዊ ኃላፊነት፣ ነፃ ምርጫ” በሚል መሪ ቃል የሚዲያ ፎረም ውይይት በታርጫ እየተካሄደ ይገኛል።

በሚዲያ ፎረም ላይ የመግቢያ ንግግር ያደረጉት የክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ የሺዋስ ዓለሙ እንደገለፁት በትምህርት ዘርፍ ላይ ትኩረት በማድረግ የአገር ብልጽግና እንዲረጋገጥ የሚያስችል ሥራ እየተሠራ በመምጣቱ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ጀምሮ የትምህርት ዘርፍ ስብራት የመጠገን ሥራ አየተከናወነ ይገኛል።

በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የትምህርት ለትውልድ ኢንሼቲቭ የማኅበረሰብ ባለቤትነትን እንዲረጋገጥ የሚያስችል ሥራ በሚዲያ በኩል በስፋት በመሠራቱ ለውጥ መመዝገቡንም አስታውቀዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ደስታ ገነመ ባቀረቡት የመወያያ ሰነድ በክልሉ አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ሀገር በቀል እውቀቶች ተቃኝተው በ10 ቋንቋዎች እንዲቀርቡ ተደርጓል።

የትምህርት ለትውልድ ኢንሼቲቭ የማኅበረሰብ ባለቤትነትን እንዲያረጋግጥ በተከናወነው ተግባር ከ1.2 ቢሊዮን ብር የሚገመት ሀብት ተሰብስቦ ለትምህርት ልማት መዋሉም ተገልጿል።

በክልሉ 60 ሞዴል ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ ሲሆን አሁን ላይ 27 ሞዴል ቅድመ አኝደኛ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውንም ዶክተር ደስታ አብራርተዋል።

ሀገር በቀል የትምህርት ቤት ምገባ አማራጭ በመፍጠር ከ67 ሺህ በላይ ተማሪዎች ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውንም በመጠቆም።

በክልሉ የጎልማሣውን ኑሮ በሚያሻሽሉና የሀገር ኢኮኖሚ የሚያሳድጉ ዘርፎችን ይበልጥ እንዲጎለብት ለማስቻል 70 ሺህ የሚደርሱ ጎልማሶች መሠረታዊ ትምህርት በመማር ላይ ይገኛሉም ብለዋል።

ካለፉት ዓመታት ይልቅ አሁን ላይ የተማሪዎች ምዘናና የፈተና ሥርዓት ከኩረጃ በጸዳ ሁኔታ እየተሰጠ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

በቀጣይም ቢሮው በትምህርት ጥራት፣ ተደራሽነት፣ ፍትሐዊነትና አካታችነት ማሣደግ፣ የመምህራንና የትምህርት አመራርን አቅም ማጎልበት፣ የመማሪያ መጻሕፍት ተደራሽነትና ጥራት ማረጋገጥ እንዲሁም የዲጂታላይዜሽንና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግ እንደሚሠራም ተገልጿል።

በክልሉ በበጀት ዓመቱ ከ8 መቶ ሺህ በላይ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ እንደሚገኙም ተመላክቷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *