የተሳለጠና ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም ዜጎች እንዲዘረጋ የትምህርት ማህበረሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ

Spread the love

የደቡብ መዕራብ ክልል ትምህርት ቢሮ ከ UNICEF ኢትዮጵያ ጋር በመሆን “የግልና የቡድን ስነ ተግባቦት ለማህበረሰብ ትስስር” ዙሪያ ለትምህርት ባለሙያዎችና ርዕሰ መምህራን በቦንጋ ከተማ ስልጠና እየሰጠ ነው።

በመድረኩ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትልና የመማር ማስተማርና ምዘና ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር ደስታ ገነመ: ቢሮ ከ UNICEF ኢትዮጵያ ጋር በመሆን በልዩ ፍላጎት ትምህርት ተግባራዊ አድርገው ውጤት እያስመዘገበ እንደሆነ ተናግረዋል።

የትምህርት ስራው አካታችና ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን እስካሁን የተከፈቱ 93 የልዩ ፍላጎት ትምህርት ማዕከላት በሙሉ አቅሙ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተሰራ ሲሆን በተያዘው በጀት ዓመት 5 ተጨማሪ ማዕከላት ተቋቁመው ወደ ስራ እንደሚገቡ ጠቁመዋል።

የአካቶ ማስተማር ስነ-ዘዴ ተግባራዊ እንዲሆን UNICEF ኢትዮጵያ የቁስና የስልጠና ድጋፍ ከማድረጉ ባሻገር ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ ተማሪዎች ወደ ትምህርት እንዲመጡና የተፋጠነ ትምህርት እንዲዘረጋ መደረጉን ዶ/ር ደስታ አክለው ገልጸዋል።

እንደ ሀገር የተጀመረው የትምህርት ጥራት ስራ እውን እንዲሆን ፕሮግራሙ ከትምህርት ሚንስትር ጋር በመሆን 1.8 ሚልዮን መጽሐፍት ታትመው ለአገልግሎት እንዲውል ማድረጉንም ተናግረዋል።

ክልሉ በኢኒሼቲቭ መልክ እየሰራ ያለውን ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስራ እየደገፈ መሆኑን የጠቀሱት ደ/ር ደስታ: ተማሪዎች ማንበብና መጻፍ እንዲችሉ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።

ፕሮግራሙ በተለያዩ ንፅህና አጠባበቅና መሰል ድጋፎች ልጆች ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመጡ እየሰራ ቢሆንም ሴት ልጆችን ጨምሮ በተለያዩ ተፅዕኖች ከትምህርት ገበታ የራቁ ልጆች ወደ ትምህርት እንዲመጡ ዜጎች የድርሻቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በዕለቱ የተገኙ ሰልጣኞች UNICEF ኢትዮጵያ ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም ዜጎች እንዲደርስ የሚያደርገውን ድጋፍ በመገንዘብ ታች ያሉ የትምህርት ማህበረሰብ ተግባራዊ እንዲያደርግ በመስራት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የክልሉ UNICEF ፕሮግራም አስተባበሪ አቶ ካሳሁን ዱባሌ እንዳብራሩት ፕሮግራሙ በሚሰራባቸው 9 ወረዳዎችና 257 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተወጣጡ የትምህርት ባለሙያዎች፣ ርዕሰ መምህራንና የተመረጡ መምህራን እየተሳተፉ ሲሆን የ UNICEF ኢትዮጵያ የማህበረሰብ ባህሪ ለውጥ ባለሙያ ሙና አህመድ እያቀረቡ ይገኛል።

በአሻግሬ ገ/ወልድ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *