





ፕሮጀክቱ በዓመት ከ2 ሚሊዮን በላይ የዓሳ ጫጩቶችን ማባዛት እንደሚያስችልም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል።
ዓሳ በውስጡ ኦሜጋ 3 የተሰኘ ፕሮትንን የያዘ በመሆኑ የምግብ እና የስነምግብ ይዘቱ ከፍተኛ ነው ያሉት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የእንስሳት እና ዓሳ ሀብት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታመነ በቀለ ይህም ለሰው ልጆች አዕምሮ ዕድገት እና ለአካላዊ ጤንነት ወሳኝ ምግብ ያደርገዋል ብለዋል።
በመሆኑም እንደ ክልል የሌማት ትሩፋት ስራ ሲጀምር በተወሰኑ አርሶ አደሮች ጓሮ የነበረውን የ1 መቶ 80 ኩሬ መጠን ወደ 1ሺህ 280 ከፍ ስናደርግ የነበረው የአርሶ አደሩ የዓሳ ጫጩት ፍላጎትና ተጠቃሚነት ወደ ፕሮጀክት ግንባታ ለመግባት አስችሎናል ብለዋል።
በተለይ እንደክልል ለነዚህ አርሶአደሮች የዓሳ ጫጩት ይቀርብ የነበረው ከሰበታ፣ ከሐዋሳ፣ ከሲዳማ ክልል አርቤጎናና ከአርባምንጭ መሆኑ ለሚመጡ የዓሳ ጫጩቶች ሞት፣ ለነዳጅ ወጪ እና ለስራ ሂደት መጓተት ምክንያት መሆኑ ለዚህ ፕሮጀክት ዕውን መሆን በር መክፈቱንም ገልጸዋል።
ይህም ለክልሉ የሌማት ትሩፋት ውጥን መሳካት ከፍተኛ ሚና የሚጫወት በመሆኑ የክልሉ መንግስት 35 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በጀት በመያዝ ወደ ግንባታ መግባቱን ጠቁመዋል።
በዚህም አሁን ላይ ግንባታው ተጠናቆ ውሃ የመያዝ ስራ ተጀምሯል ያሉት አቶ ታመነ በቀለ በቅርቡ ተመርቆ የዓሳ ጫጩት ለማስገባት መሰናዳቱንም ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ የዓሳ ጫጩትን ቁጥር በውል ለማወቅ የሚያስችል ዘመናዊ የዓሳ ጫጩት ማስፈልፈያ ማሽን የሚገጠምለት በመሆኑ ከሌሎች መሰል ፕሮጀክቶች ለየት ያደርገዋል ያሉት ኃላፊው ይህም በዓመት ከ2 ሚሊዮን በላይ የዓሳ ጫጩቶችን ለማባዛት ያስችለዋልም ብለዋል።
ለጊዜው በአካባቢው የሚላመዱና አዋጭነታቸው በተረጋገጡ ቲላፒያ እና ካርፕ በተሰኙ ሁለት የዓሳ ዝሪያዎች ስራው እንደሚጀመርም ገልጸዋል።
ይህም በፕሮጀክቱ አካባቢ ለሚገኙ ወጣቶች በቋሚነትም ሆነ በጊዜያዊነት በርካታ የስራ ዕድል ይዞ እንደሚመጣ የጠቆሙት አቶ ታመነ በየደረጃው ከፕሮጀክቱ ዓሳ ጫጩት ተቀብለው ከሚያራቡ ጀምሮ በክልሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አርሶአደሮችን ተጠቃሚነት ያረጋግጣልም ብለዋል።
ይህም በምግብ እና ስነምግብ የበለጸገ ትውልድ በመፍጠር የመቀንጨር አደጋን የሚታደግ በመሆኑ የክልሉ አርሶአደሮች በየጓሯቸው ትናንሽ የውሃ ኩሬዎችን በማዘጋጀት የዓሳ ጫጩቶችን ለመቀበል ከወዲሁ መዘጋጀት እንዳለባቸውም አቶ ታመነ አሳስበዋል ሲል የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ ዘግቧል።
