







የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ግብርና ቢሮ የቡና፣ ሻይ ቅመማ ቅመም ባለስልጣን በደረቅ ቡና ምርት አዘገጃጀትና ግብይት ለዞን እና ወረዳ ባለድርሻ አካላት በሚዛን አማን ከተማ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል ።
በስልጠናው ላይ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር እና የልማት ጥበቃ ዘርፍ ኃላፊ አቶ በላይ ኮጁአብ ዘርፉ ትልቅ የሀገር ኢኮኖሚና የክልሉን ከፍተኛ ኢኮኖሚ የማመንጨት ድርሻ ስላለው በትኩረት መሰራት እንደሚገባ ገልጸዋል ።
የቡና ስራ የቡና ለቀማ ወቅቱ ከደረሰ በኃላ የሚሰራ ብቻ ሳይሆን ጥራቱን በማስጠበቅ በክልሉ ብሎም በሀገርቱ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ በአግባቡ ለማስግኘት ዓመቱን ሙሉ የሚሰራ መሆኑን በመግለጽ የእስካሁን አፈጻጸም በመገምገም በዘርፉ በምርት አዘገጃጀትና ጥራት ላይ የሚያጋጥሙ ማነቆዎችን ለመፍታት ስልጠናው ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል ።
አክለውም ክልሉ ከ532,139 ሄ/ር ሽፋን፣ ከ300,000 ሄ/ር በላይ ምርት የሚሰጥ እናት ቡና መኖሩን እንዲሁም በምርታማነት ባለፉት ሦስት ዓመታት ክልሉ ከነበረበት 35,000 ቶን በአማካይ ወደ 54,000 ቶን ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ መቻሉን እንዲሁም በያዝነው ዓመት 67,887 ቶን ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅደው እየሰራ መሆኑን አቶ በላይ አንስተዋል ።
በመጨረሻም በክልሉ የቡናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ ቢሆንም በክልሉ ካለው ዕምቅ አቅምና የማሳ ሽፋን አንጻር ምርታማነትን በማሳደግ ጥራት ያለው ቡና ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ ገቢን ከመሰብሰብ አንጻር ውስንነት በመኖሩ የሁሉም የባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደሚያስፈልግ በአጽንኦት አሳስበዋል ።
የስልጠና ሰነዱና የ2017 ዓ/ም የ2ኛ ሩብ ዓመት የአፈፃፀም ሪፖርት ለውይይቱ መነሻነት በክልሉ የቡና፤ ሻይ ቅመማ ቅመም ባለስልጣን የቡና ምርት ዝግጅትና ገበያ ልማት ዘርፍ ተወካይ በሆኑት በአቶ መስፍን ኃ/ማሪያምና የቡና ቁጥጥር ባለሙያ በአቶ ጣሃ አህመድ ለሰልጣኞች እየቀረበ ይገኛል ።
በስልጠናው የክልሉ ባለስልጣን መ/ቤት ም/ዋና ዳይረክተሩን ጨምሮ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ የየዞኑ ግብርና የተፈጥሮ ሀብትና ህብረት ስራ መምሪያ ኃላፊዎች፣ ከዞንና እና ከወረዳ የመጡ የዘርፉ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ሲሆን ለሁለት ተከታታይ ቀን እንደሚቆይ የወጣው መርሃ ግብር ያስረዳል።
በጌታሁን ግርማ
