




የግንባታ ማስጀመሪያ የውል ፊርማ ሥነ-ሥርዓት ላይ የግንባታዉ የሥራ ተቋራጮች ከክልሉ መንግስት ጋር ውል ተፈራርመዋል።
እነኚህ በመጀመሪያው ምዕራፍ የሚገነቡ በአራቱ ብዝሃ ዋና ከተሞች የሚገነቡ ግንባታዎች በቦንጋ ማዕከል የፕሬዝዳንቱ እና የክልል ተቋማት ቢሮ ህንፃ፣ በታርጫ ከተማ የክልል ተቋማት ቢሮ ህንፃ፣ በሚዛን አማን ከተማ የክልል ተቋማት ቢሮ ህንፃ እና በቴፒ ከተማ የክልል ተቋማት ቢሮ ህንፃዎች ናቸዉ።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) የቢሮ ህንጻዎች ግንባታ ማስጀመሪያ የውል ፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ባለፉት ሁለት ዓመት ተኩል ጀምሮ በክልሉ ብዝሃ ዋና ከተሞች ለሚገነቡ አምስት ግዙፍ ህንጻዎች የዲዛይን ዝግጅት እና አስፈላጊ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን እና የጨረታ ሂደቱም ከምንም ቅሬታ ነጻ በሆነ ሁኔታ መከናወኑን አስረድተዋል።
ለቢሮ ህንጻዎቹ ግንባታ 5.763 ቢሊዮን ብር በጀት የሚፈጅ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።
የህንጻዎቹ ግንባታ በሁለት ዓመታት ውስጥ እንደሚጠናቀቁም ጠቁመዉ ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ ውስጥ ጥራታቸውን እና ደረጃቸው ጠብቆ እንዲከናወኑ አማካሪዎች እና ተቋራጮች የአጋርነት ድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የህንጻ ግንባታ ስራዉን ከሚቀጥለዉ ሳምንት ጀምሮ ወደ ሥራ እንዲገቡ የሚደረግ ሲሆን ከወዲሁ መጠናቀቅ ያለባቸዉ የቦታ ዝግጅት ሥራዎች ትኩረት ተደርገው እንዲከናወኑ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር እንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ አሳስበዋል።
የግንባታ ሂደት የማማከር አገልግሎቱንም የክልሉ ግንባታ ዲዛይንና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን ከኦሮሚያ ኢንጀነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር በቅንጅት ይመረዋል ።
የፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው፣ የክልሉ አስፈጻሚ አካላትና ሌሎች የክልል ቢሮ ኃላፊዎች፣ የግንባታ ሥራ ተቋራጮችና አማካሪዎች እንዲሁም የየቢሮዎቹ ህንጻዎች የሚገነቡበት ዞኖችና የከተማ አስተዳደር ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በፍቅር ከበደ
