

ኢትዮጵያ በዘላቂ ሰላም እንዳትኖር እንቅፋት የሆኑባትን መሠረታዊ ምክንያቶች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ በምክር ቤት ባደረጉት ንግግር በዝርዝር አብራርተዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፃ፣ ለሰላም እጦት ቀዳሚው ምክንያት ልዩነቶችን በኃይል ብቻ የመፍታት ከጥንት ጀምሮ የቆየው የተሳሳተ ልምምድ ነው ብለዋል።
ይህ ባህል ለውይይትና ለሰላማዊ መፍትሄዎች ዕድል በመንፈግ ሀገርን በግጭት አዙሪት ውስጥ እንድትቆይ አድርጓታል ነው ያሉት።
በሁለተኛ ደረጃ አሁንም ድረስ የሀገርን ሕልውና እየተፈታተነ የሚገኘው ከጥንት ጀምሮ የተወረሰው የ”ባንዳነት” ልምምድ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህም ለሀገር ውስጣዊ ሰላም ትልቅ ስጋት መሆኑን አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም የውጭ ጠላቶች የኢትዮጵያን ማደግና መጠናከር እንደ ስጋት በመቁጠር፣ ስኬቷን ለማደናቀፍ የሚያደርጉት ያልተቋረጠ ጥረት ለሰላማችን መታወክ ሦስተኛው ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።
እነዚህን የታሪክ ጠባሳዎችና የቆዩ ስልቶችን በጋራ በመመከት ለሀገር ዘላቂ ሰላም መቆም እንደሚገባም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ኢቢሲ ዶትስትሪም – የመረጃዎ ድልድይ! ሙሉውን ዘገባ እና ዝርዝር መረጃዎችን በኢቢሲ ዶትስትሪም ዲጂታል አማራጮች ይከታተሉ።
