
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ስላለው ወቅታዊ ግንኙነት ለምክር ቤቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ችግር መነሻ የቀይ ባሕር ጥያቄ ሳይሆን፣ ኤርትራ ሀገር ሆና ከተመሰረተችበት ጊዜ ጀምሮ የነበረ ታሪካዊ ሂደት መሆኑን ገልጸዋል።
በለውጡ ማግስት በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረው የዓመታት ችግር እንዲፈታ መንግሥታቸው ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም፣ ሂደቱ በተፈለገው ልክ እንዳልተሳካ ጠቁመዋል። በተለይም በሰሜኑ ጦርነት ወቅት የታዩ ክስተቶች ለቅራኔው መፋፋም ምክንያት መሆናቸውን በሚከተሉት ነጥቦች አብራርተዋል::
የኤርትራ ሠራዊት በጦርነቱ ወቅት ሽረ ገብቶ ንብረት መዝረፉን፣ እንዲሁም በአክሱም በዜጎች ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ መፈጸሙን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዝርዝር አስታውሰዋል።
በአዲግራት እና በዓድዋ የሚገኙ ፋብሪካዎችን ነቅሎ እስከ መውሰድ የደረሰ ድርጊት መፈጸሙን ገልጸው፤ በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት በብዙ አቅጣጫዎች ተወጥሮ የነበረበት አስቸጋሪ ጊዜ እንደነበር ገልጸዋል።
ችግሩን በውይይት ለመፍታት የቀድሞውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን እስከ መላክ የተደረገው ጥረት ፍሬ አለማፍራቱን ጠቁመዋል።
ወደ መቐለ ይደረግ የነበረው ጉዞ የዘገየው የኤርትራን ሠራዊት ከጀርባ ለመግታት እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ልዩነቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው የትግራይ ሕዝብ እፎይታ ያገኘበት የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ መሆኑን ገልጸዋል።
