ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በቦንጋ ከተማ የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶችን በመጎብኘት የአፈጻጸም ክፍተቶች እንዲታረሙ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በቦንጋ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት፣ የማረሚያ ተቋም እና የቦንጋ ዘመናዊ መናኸሪያ የግንባታ ሂደትን በዛሬው ዕለት ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

በክልሉ መንግሥት በከፍተኛ በጀት ግንባታው እየተከናወነ የሚገኘው የቦንጋ መናኸሪያ የመጀመሪያው ምዕራፍ የአስፋልት ንጣፍ ሥራ አሁን ላይ እየተገባደደ ሲሆን፣ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን ተገልጿል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በጉብኝታቸው ወቅት እንደተናገሩት፤ ቀደም ሲል በፕሮጀክት አስተዳደር ረገድ የሚታዩ ደካማ አፈጻጸሞችና የአሰራር ክፍተቶች ግንባታው እንዲዘገይ አድርገውት የነበረ ቢሆንም፣ በየጊዜው በሚደረግ ጥብቅ ክትትል ችግሮቹ ተፈተው ፕሮጀክቱ አሁን ላለበት የተሻለ ደረጃ መድረስ ችሏል።

የልማት ፕሮጀክቶች ጥራታቸውን ጠብቀውና በታቀደላቸው ጊዜ ተጠናቅቀው ለህዝብ አገልግሎት እንዲውሉ የክልሉ መንግስት በቁርጠኛነት ይከታተላል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣

በቀጣይም በፕሮጀክት አፈጻጸም ላይ የሚታዩ ማነቆዎች የባለድርሻ አካላት በመቀናጀት በፍጥነት ማረም እንደሚገባ አሳስበዋል።

የማረሚያ ተቋም ግንቦታ አፈጻጸም በጥሩ ደረጃ ላይ እንዳለ የተመላከተ ሲሆን ቀሪ ስራዎችን በማጠናቀቅ ለአግልግሎት ብቁ እንዲኾን በቂ የግንባታ ግብዓት መቅረብ እንዳለበትም ተጠይቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *