



የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ዋና ኦዲት መ/ቤት የ2016 በጀት ዓመት የኦዲት አፈጻጸሙን ለክልሉ ም/ቤት አቅርቧል ።
የዋናው ኦዲት መስሪያቤት የአፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት ዋና ኦዲተር አቶ አስራት አበበ በበጀት ዓመቱ በፋይናንሻልና ህጋዊነት፣ 1ኛ ዙር ኢንቲሪም ኦዲት፣የክልሉ የተጠቃለለ ገቢና ወጪ ኦዲት፣የክዋኔና አካባቢ ጥበቃ ኦዲት ጭብጦች፣በልዩ ኦዲት፣በገቢና የንብረት ኦዲቶች ላይ ትኩረት በማድረግ መሰራቱን አብራርተዋል ።
በክዋኔ ኦዲት ስራዎች በተመረጡ ፕሮጀክቶች አካባቢ በመውረድ የፊዚካልና ፋይናንሻል አፈጻጸማቸው ያለበትን ደረጃ በመፈተሽ የሚታዩባቸው ጉድለቶች እንዲታረሙ ፕሮጀክቶችን ለሚመሩ ተቋማት የእርምት አስተያየት መሰጠቱን ተናግረዋል።
በከተሞች እየተስተዋለ ያለው የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ስርዓት በአካባቢው ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ኦዲት በማድረግ በዚህ ዘርፍ የወጡ ህጎች ተፈጻሚ ስለመሆናቸው ክትትል መደረጉን አብራርተዋል ።
የክልሉ መንግስት ከፍተኛ ሀብት ከሚያፈስባቸው ዘርፎች አንዱ በሆነው በንብረት ግዢ ላይ የንብረት አስተዳደር ህግን ተከትለው ስለመፈጸማቸው በተመረጡ ሸካና ምዕራብ ኦሞ ዞኖች ከ2013_2014 ዓ/ም ድረስ ባለው የንብረት አያያዝ ላይ የአሰራር ስርዓቱን ያልተከተሉ አሰራሮች መታየታቸውን በሪፖርቱ አመላክተዋል።
ከህብረተሰቡ ከሚቀርቡ ጥያቄና ጥቆማ በመነሳት ከመደበኛ ኦዲት ውጪ የልዩ ኦዲት ስራዎችን መስሪያቤቱ ማከናወኑን አቶ አስራት አበበ ተናግረዋል።
በዳዉሮ ዞንና በቤንች ሸኮ ዞን ለታላቁ ህዳሴ ግድብ የተዋጣውን የሂሳብ እንቅስቃሴዎች መረጃ በመቃኘት ከተሰበሰበው ሀብት ውስጥ ወደ ህዳሴ ግድብ በተከፈተው የባንክ አካውንት ገቢ ያልተደረጉ ሀብቶች መኖራቸው በቀጣይ የሀብት አሰባሰብ ላይ ስጋት መሆኑን በሪፖርቱ አመላክተዋል።
ለታላቁ ህዳሴ ግድብ የሂሳብ እንቅስቃሴ ኦዲት በሚደረግበት ጊዜ መረጃዎችን አቅርቦ ኦዲት ለማስደረግ ያለው ማነቆ ከፍተኛ መሆኑንም አቶ አስራት አብራርተዋል ።
የፋይናንሻልና ህጋዊነት ኦዲት ከማካሄድ አንጻር የጥሬ ገንዘብና የባንክ ሂሳብ አስተዳደር ኦዲት በማድረግ በ11 መ/ቤቶች በጥሬ ገንዘብ ሪፖርትና በካዝና ቆጠራ መካከል የጥሬ ገንዘብ ልዩነት በማነስ መታየቱን እንዲሁ ገልጸዋል።
ዋና ኦዲት መ/ቤቱ በዚህ ዘርፍ በ32 ተቋማት ላይ የኦዲት ስራዎችን ያከናወነ ሲሆን ከበጀት አጠቃቀም አንጻር ጉድለት የሚታዩባቸው ተቋማት የአሰራር ስርዓቱን ተከትለው በጀትን እንዲመሩ ለተቋማቱ የእርምት አስተያየት መሰጠቱንም ጨምረው ገልፀዋል ።
ህግና መመሪያን ያልተከተሉ ወጪዎች፣ ክፍያዎች፣ አሠራርን ያልተከተሉ የሂሳብ አመዘጋገቦች፣ በጊዜያቸው መከፈል የነበረባቸውና ያልተከፈሉ ሂሳቦች መኖር፣የነዳጅና ቅባት ግዢዎች ላይም የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ያካተተ ሪፖርትም በአቶ አስራት ቀርቧል ።
በቀረበው ዝርዝር የክልሉ ዋና ኦዲት መ/ቤት ሪፖርት ላይ ከም/ቤት አባላት የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ቀርበው በአቶ አስራት አበበ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።
የተለያዩ ጉድለቶች በታዩባቸው ተቋማት እና አካላት ላይ ተጠያቂነትን በማስፈን ም/ቤቱም ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት አስፈላጊውን የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስዱ ዋና ኦዲተር አቶ አሰራት አበበ ጠይቀዋል ፡፡
የክልሉ ዋና ኦዲት መ/ቤት ያቀረበውን የ2016 በጀት ዓመት ሪፖርት የምክርቤት አባላት በሙሉ ድምጽ አጽድቀዋል ።
በታጠቅ አበበ
