በክልሉ በ2016 በጀት ዓመት በ14 ወረዳዎች ላይ የመሬት ልኬት ስራ መሰራቱ ተገለጸ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ግብርና ቢሮ የ2ኛ ደረጃ የገጠር መሬት ልኬት ካርታና የይዞታ ማረጋገጫ የደብተር ስርጨት መርሃ ግብርን በካፋ ዞን ጠሎ ወረዳ ያማ ቀበሌ አካሂዷል፡

በመድረኩ የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትልና የተፈጥሮ ሃብትና መሬት አስተዳደር ዘርፍ ሃላፊ አቶ ውብሸት ዘነበ በክልሉ በ2016 በጀት ዓመት በ14 ወረዳዎች የመሬት ልኬት ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

የመሬት ልኬት መሰራት ከመሬት ጋር ተያይዞ ይነሱ የነበሩ የድንበር ግጭቶችንና ቅሬታዎችን ከመፍታት ባሻገር ፍትሃዊነትና እኩልነት የሰፈነበት መሬትን የመጠቀም መብት ያረጋግጣል ብለዋል፡

የመሬት መረጃን ማዘመን አርሶ አደሩ በወሰን ግጭቶች ምክንያት ፍትህ ፍለጋ በመመላለስ የሚያባክነውን ጊዜ በማክሰም አርሶ አደሩ ድንበሩን አውቆና የእኔነት ስሜት አድሮበት መሬቱን በመንከባከብ አልምቶ የሚጠቀምበት ፣ ካርታውን አስይዞ ከባንክ ለመበደር የሚያስችለው ከሃብቶች ሁሉ በላይ የሆነ አንጡራ ሀብት እንደሆነም አቶ ውብሸት ዘነበ በንግግራቸው ጠቅሰዋል፡

አክለውም በጠሎ ወረዳ የመሬት ልኬት ለተደረገላቸው 24 ቀበሌዎች ለሁሉም ስርተፊኬትና ደብተር የተዘጋጀላቸዉ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ አርሶ አደሩ በካርታው ከባንክ ብድር የሚያገኝበት ስራ ይሰራል ብለዋል።

መሬት ተቆጥሮ መረጃ ሲያዝ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንደሚኖሩት የገለጽት የካፋ ዞን ግብርና ደን አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ጋዎ አባመጫ አርሶ አደሩ መሬቱን የመንከባከብ ግዴታ ያለበት እንደሆነና መብትና ግዴታውን ለይቶ መሬትን ሊጠቀም እንደሚገባም አሳስበዋል።

በጠሎ ወረዳ በሚገኙ በ24 ቀበሌዎች ሙሉ በሙሉ የመሬት ልኬት ስራ መጠናቀቁን የተናግሩት የጠሎ ወረዳ ግብርና ደን አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ልማት ጽ/ ቤት ኃላፊ አቶ አፈወርቅ አደመ በዚህም 12ሺ567 አባዎራዎች 1ሺ188 እማዎራዎች እንዲሁም 729 የመንግስት ተቋማትና 211 የወል መሬቶች በድምሩ 14ሺ095 የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ተጠቃሚ እንድሆኑ በመደረጉ በቀድሞ 22 ሺህ 518 የነበረው በአዲሱ ልኬት 32 ሺህ 548 ሄክታር ሆኖ ተመዝግቧል ብለዋል፡

በመሬት ልኬት ሂደትም CALM.LA ፕሮግራም ከ4 ሚሊዬን በላይ በጀት መድቦ ድጋፍ ያደረገ መሆኑም ተገልጿል ።

በመድረኩ የክልል የዞንና የወረዳ አመራሮችና የዘርፉ ባለሙያዎች በተገኙበት የይዞታ ማረጋገጫ ሰርትፊኬትና ደብተር ተሰጥቷቸዋል፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *