











የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የ2016 በጀት ዓመት የክልሉ ፍርድ ቤቶች የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርቧል።
ዝርዝር የበጀት ዓመቱ ሪፖርትና የ2017 በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅድ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቆጭቶ ገብረማርያም የቀረበ ሲሆን የምክር ቤቱ አባላት በቀረበው ረፖርት ላይ ሀሳብ አስተያየት ሰንዝረዋል።
በየደረጃው የሚገኙ ፍርድ ቤቶች ቀልጣፋ፣ ግልፅ፣ ተገማች፣ ሚዛናዊና ተደራሽ የሆነ ዳኝነት አገልግሎት ለህብረተሰቡ የመስጠት ተልዕኮ በመያዝ በመልካም አስተዳደርና በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት የሚኖራቸውን ዓይነተኛ ሚና እንዲወጡ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነው ፕሬዚዳንቱ የገለጹት፡፡
ፍርድ ቤቶች ነጻና ገለልተኛ ሆነዉ የዳኝነት አገልግሎት በመስጠት የመንግሥት የተፋጠነ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ፣ የዲሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ግንባታ ዕቅዶች እንዲሳኩ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ የገለጹት አቶ ቆጭቶ በየደረጃዉ የሚገኙ የክልሉ ፍርድ ቤቶች የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ፣ የህግ በላይነት እንዲረጋገጥ፣ ለክልሉ ልማትና ዕድገት የሚጠበቅባቸዉን ድርሻ እንዲወጡ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በበጀት ዘመኑ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍናንና ዉጤታማነትን በማሳደግ፣ የዳኝነት ነፃነት እና ተጠያቂነት በማረጋገጥ ፣ የአገልግሎት ተደራሽነትን ማስፋት መቻሉን የገለጹቱ ፕሬዝዳንቱ ተቋማዊ መፈጸምና ማስፈጸም አቅም ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል።
በዚሁ መሰረት የ2016 በጀት ዓመት በየደረጃው ባሉት ፍርድ ቤቶች 70ሺህ 385 መዝገቦች ላይ ውሳኔ መተላለፉንና ይህም አጠቃላይ ከቀረቡ መዝገቦች 97.3 ከመቶ መሆኑን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ የተገኙ ውጤቶችን በማስቀጠል የተገልጋይ እርካታን ለማሳደግ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎችን በማጠናከር የፍርድ ቤት አሠራርና አደረጃጀቶች ማሻሻልና በስዉ ኃይልና በሀብት ማጠናከር በትኩረት ይሠራልም ብሏል ፕሬዚዳንቱ።
በመሆኑም በቀጣይ ዓመት መልካም አፈጻጸሞችን በማስቀጠልና በድክመት የታዩ አፈጻጸሞችን በማሻሻል በቀጣዩ በጀት ዓመት ላቅ ያለ ውጤት ለማስመዝገብ ትኩረት መደረጉን አብራርተዋል።
የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው የዳኞች የሙያ ነጻነትን በማረጋገጥ የአቅም ግንባታ ስለጠናና የትምህርት ዕድል በማመቻቸት በተመደቡበት ተረጋግተው እንደሰሩ ማድረግ እንደሚገባ በመግልጽ የተገልጋዩች እርካታን ለማሳደግ የተጀመረውን ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ምክር ቤቱ የክልሉን ጠቅላይ ፍ/ቤት ሪፖርት አድምጦ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።
በዕድገቱ በዛብህ
