




የጤና ሚኒስቴር ያዘጋጀው አገር አቀፍ የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት ፕሮግራም የስድስት ወራት አፈጻጸም የግምገማ መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።
የግምገማ መድረኩ ማጠናቀቂያ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ እንደተናገሩት እንደ ሀገር ጠንካራ የጤና ሥርዓት በመገንባት የአገልግሎት ጥራትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለው የማህበረሰቡን የጤና አገልግሎት ፍላጎት ለማሻሻልና የሆስፒታሎችን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት ፕሮግራም ጉልህ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት ፕሮግራም መርሃ ግብር ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ተቀርፆ 4ኛው ምዕራፍ ድረስ በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው ፕሮግራሙ በሆስፒታሎች መካከል ጠንካራ ትስስርና መደጋገፍን በመፍጠር የህብረተሰቡን የህክምና የአገልግሎት ፍላጎት እርካታ ለማሳደግ ምቹ አሰራርን እንደፈጠረ ተናግረዋል።
ዶ/ር መቅደስ አያይዘውም ፕሮግራሙ እንደ ሀገር ያለንን የሰው ሀይልና የህክምና መሳሪያዎች በጋራ በመጠቀም የማህበረሰቡን የአገልግሎት ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ እንዳሻሻለው አክለው 4ኛው ምዕራፍ ከመጠናቀቁ በፊት የተጀመሩ መልካም ስራዎችን በፍጥነት በማጠናቀቅ እውቅና የሚሰጣቸውን ክልሎችና ሆስፒታሎች የመለየት ስራ እንደሚሰራም አብራርተዋል።
በመርዓ ግብሩ በርካታ በክረምትና በመደበኛው የአገልግሎት አሰጣጥ ጊዜያት የበጎ ፈቃድ ቀዶ ሕክምና እና ሌሎች የህክምና አገልግሎት በቅንጅት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ውጤታማ መሆኑን እና በሆስፒታሎች መካከል በመረጃ ላይ የተመሰረተ የህክምና “ሪፈረል” ቅብብሎሽን ለማሳለጥ አስፈላጊ እንደሆነ ጠቅሰው በሁሉም ክልሎችና የህክምና ተቋማት የተጀመሩ በጋራ የመስራትና የመደጋገፍ ተግባራት ወደፊትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በጤና ተቋማት እና የጤና አገልግሎት መስጫ ቦታዎች ላይ ከንጽህና ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለማሻሻልና ምቹና ጽዱ የሆኑ ጤና ተቋማት ለመፍጠር ሚኒስቴር መ/ቤቱ የጽዱ ጤና ተቋም ኢኒሼቲቭ ቀርፆ በመተግበር ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው፤ ጤና ተቋማት የማህበረሰቡን የአገልግሎት ፍላጎትና እርካታ በተጨባጭ ለማረጋገጥ ውጤታማ የሆነ ስራዎችን መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረው ፤ የህክምና አገልግሎት ተደራሽነትንና ጥራትን ለማረጋገጥ የዘርፉን የህክምና ግብዓትና መሠረተ ልማት ለማሟላት ሚኒስቴር መ/ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በፕሮራሙ የተገኙ ስኬቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ ቀጣይነት እንዲኖረው ይሰራል ብለው በሀገሪቱ ጠንካራ የጤና ሥርዓት ለመገንባት በሚደረገው እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት መርሃ ግብር ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ በንግግራቸው አክለዋል።
ዶ/ር ኢሊባቦር ቡኖ በጤና ሚኒስቴር የሜዲካል አገልግሎት መሪ ስራ አስፈጻሚ በመልዕክታቸው የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት መርሃ ግብር 4ኛው ምዕራፍ ሲጠናቀቅ እውቅናና ሽልማት የሚሰጣቸው ጤና ተቋማት ተለይተው እውቅና እንደሚሰጣቸው አንስተው ለ5ኛው ዙር ምዕራፍ ዝግጅት የሚደረግበትና ወደስራ የሚገባበት ወቅት በቅርቡ እንደሚጀመር በመልዕክታቸው ጠቁመዋል።
በግምገማ መድረኩ ማጠቃለያ ላይ የሰርጂካል ባክሎግ ክሊር ለማድረግ የሁሉም ክልሎች ጤና ቢሮ ኃላፊዎችና ተወካዮች በተገኙበት በቀጣይ በቅንጅትና በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን የስምምነት ሰነድ የፊርማ ስነ ስርዓት ከጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ ጋር ተፈራርመዋል።
በፕሮግራሙ ላይ የጤና ሚኒስቴር አመራሮችና ባለሙያዎች፣ የሁሉም ክልሎች የጤና ቢሮ አመራሮችና ባለሙያዎች፣ በየደረጃው የሚገኙ የሆስፒታል የሥራ ኃላፊዎች እና ሌሎች የአጋርና ባለድርሻ አካላት ተወካዮች በተገኙበት የስራ አፈጻጸም ሪፓርትና ምርጥ ተሞክሮዎች ቀርበው ውይይትና ሀሳብ ተሰጥቶበታል።
መረጃው የክልሉ ጤና ቢሮ ነው።
