







የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት የውሃ ማዕድን እና ኢነርጂ ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀምና ጉባኤና የቀሪ 3 ወራት የትኩረት አቅጣጫ ላይ የምክክር መድረክ በቦንጋ እያካሄደ ነው።
በጉባኤው የተገኙት የክልሉ የመንግስት ረዳት ተጠሪና የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ነጋ አበራ ክልሉ ከተመሠረተ ወዲህ በዘርፉ ለውጥን ሊያመጡ የሚያስችሉ በርካታ መሠረታዊ ዕድገት ተኮር የሆኑ ተግባራት በመከናወናቸው የውሃ ሽፋንና ተጀራሽነት ላይ ዕመርታዊ ለውጥ መምጣቱን ተናግረዋል።
አክለውም ተቋሙ ለዜጎች መሠረታዊ ፍላጎትን ከማሟላትም በላይ በአጭር ጊዜ ከድህነትና ተረጂነት ለማላቀቅ፣ የስራ ዕድልን ለመፍጠርና በሀገሪቱ ኢኮኖሚ የድርሻውን ለመወጣት የመስኖ አውታሮችን በማቅረብ፣ የማዕድን ዘርፉን በማነቃቃት ወደ ስራ በማስገባት ከፍተኛ ሚና የሚጫወትና እየተጫወተ ያለ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም በዘርፉ ሁለንተናዊ ብልጽግናን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የተገኙ ውጤቶችን ለማላቅ፣ የስራ ዕድልን በሰፊው ለመፍጠር፣ የአገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል የመልካም አስተዳደር ችግር መፍታት፣ ብሎም ከውጪ ለግብዓትነት በከፍተኛ ወጪ የሚገቡት እንደ ድንጋይ ከሰል ያሉትን በሀገር ውስጥ ለመተካትና የወጭ ምንዛሪን ለማሳደግ በቅንጅትና በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ በአጽንኦት ተናግረዋል።
በጉባኤ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር በየነ በላቸው ክልላች በርካታ የገጸ ምድርና ከርሰ ምድር የውሃ ሀብት ቢኖረዉም ክልሉ ከመመስረቱ በፊት ዘርፉ ብዙ ትኩረት ያልተሰጠበት መሆኑን በማስታወስ አሁን ዕምርታዊ ለውጥ መምጣቱን አንስተዋል ።
ከክልሉ መመስረት ወዲህ ያለውን አቅሞችን በመለየት ኃይልን በማሰባሰብ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በተሰራው መጠነ ሰፊ ስራ ክልሉ ሲመረት የክልሉ የመጠጥ ውሀ ሽፋን 32.7% ላይ የነበረው እንደሆነ በማስታወስ ነባር ተጀምሮ ያልተጠናቀቁና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በትኩረት በማጠናቀቅ የክልሉን የውሀ ሽፋን 43.73% በማድረስ ከ450 ሺህ በላይ ህዝብን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል ።
በተጨማሪም ከ150 ሺ በላይ ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች በግንባታ ሂደት ላይ መሆኑንና 10 የከተማ ውሃ ጥናት ላይ መሆኑን አንስተዋል።
በመስኖ ዘርፍ በክልሉ ውስጥ የመንግስት፣ የህብረተሰብና የልማት አጋሮችን ቅንጅት ግንባታው 15 መለስተኛ የመስኖ አውታሮችን በመገንባት 3627 ሄ/ር ማልማት ወደሚችልበት ደረጃ ክልሉ መድረሱንና የመስኖ ተቋማትን ወደ 77 ከፍ ማለቱ እንዲሁም ከ15 በላይ ፕሮጀክቶች በግንባታ ሂደት ላይ መሆኑን የቢሮ ኃላፊው አንስተዋል ።
በመጨረሻም የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን በጋራ የሚገነቡ በመሆኑ ከዞንና ወረዳዎች የሚለቀቀው የማቺንግ ፈንዲ በጊዜ ገቢ ባለመደረጉ የክልሉን የውሃ አቅርቦት ስርዓትና የውሃ ሽፋንን ለማሳደግና ግንባታውን ለማጠናቀቅ ማነቆ መሆኑን በማንሳት ተሳታፊዎች በትኩረት እንዲወያዩ አሳስበዋል ።
የቢሮ የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት በኢንጅነር ፈልታሞ ዲብሎ ለተሳታፊዎች እየቀረበ ይገኛል ።
በጌታሁን ግርማ
