ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን የኃይል ተቋማት ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት ለ10 ቀናት እንዲቆም አዘዙ

Spread the love

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን የነዳጅ እና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ተቋማት ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች ለ10 ቀናት እንዲቋረጡ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

ትራምፕ ይህንን ውሳኔ ያስተላለፉት በቴህራን በኩል በቀረበ ጥያቄ መሠረት መሆኑን ቢገልጹም በጉዳዩ ላይ ከኢራን በኩል የተሰጠ ይፋዊ ምላሽ የለም።

ፕሬዚዳንቱ ከኢራን ጋር እየተደረገ ያለው ድርድር በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ አንድ የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣን ግን የአሜሪካ የሰላም ዕቅድ “አድሏዊ እና ፍትሐዊ ያልሆነ” ሲሉ አጣጥለውታል።

ይህ ጦርነት በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ከመቅጠፉ ባለፈ፣ የዓለም የነዳጅ ዋጋ በ40 በመቶ እንዲያሻቅብ እና የማዳበሪያ ዋጋ በግማሽ እንዲጨምር በማድረግ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል።

በሌላ በኩል አሜሪካ በኢራን ላይ የምታደርገውን ወታደራዊ ግፊት ለመጨመር ለመጀመሪያ ጊዜ በጦርነት ውስጥ ሰው አልባ ፈጣን ጀልባዎችን ለጥበቃ ሥራ ማሰማራቷን የፔንታጎን መረጃ ያመለክታል።

ኢራን በበኩሏ በሆርሙዝ የባሕር ላይ መተላለፊያ በኩል የሚደረገውን የነዳጅ ንግድ እንቅስቃሴ በከፊል ማገዷን እንደቀጠለች ነው።

አሜሪካ በፓኪስታን በኩል የላከችው ባለ 15 ነጥብ የሰላም የመፍትሔ ሐሳብ የአሜሪካን እና የእስራኤልን ጥቅም ብቻ የሚያስጠብቅ ነው በሚል በቴህራን ተቀባይነት አላገኘም።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ካልከፈተች እና የኒውክሌር መርሐ-ግብሯን ካላቆመች “ከባዱ ቅዠት” እንደሚሆን አስጠንቅቀዋል።

ጥቃቱ እስከ ሚያዝያ 6 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ እንዲቆም የተወሰነ ቢሆንም፣ የዲፕሎማሲው ጥረት አሁንም ቀጥሏል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *