ስታርት አፖችን በፋይናንስ መደገፍ የሚያስችሉ አሠራሮች ተዘርግተው ተግባራዊ እየተደረጉ ነው – የኢትዮጵያ ልማት ባንክ::

Spread the love

በኢትዮጵያ በስፋት የተጀመሩ ስታርት አፖችን በፋይናንስ መደገፍ የሚያስችሉ አሠራሮች ተዘርግተው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አስታወቀ።

በሳይንስ ሙዚየም የተከፈተውን ስታርት አፕ ኢትዮጵያ አውደ-ርዕይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጨምሮ በርካታ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ምሁራንና ተማሪዎች እንዲሁም የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጎብኝተውታል።

ከመጋቢት 30 እስከ ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም ለሕዝብ ዕይታ ክፍት በተደረገው አውደ-ርዕይ በመጀመሪያ ደረጃ በምርት ሙከራና ምርት ወደ ገበያ ማቅረብ የጀመሩ ስታርት አፖች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

በአውደ-ርዕዩ ከጉብኝት በተጓዳኝ ሁነቱን የተመለከቱ መድረኮች እየተዘጋጁ የዘርፉ ምሁራንና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እየመከሩበት ይገኛል።

የባንክ ዘርፎች ለስታርት አፕ የፋይናንስ ድጋፍ እየሰሩበት ስላለው አግባብ ትኩረት ያደረገ የፓናል ውይይት በተካሄደበት ወቅት የተለያዩ ባንኮች የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ታድመዋል።

በመድረኩ ከተሳተፉት መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዮሐንስ አያሌው(ዶ/ር)፤ ልማት ባንክ በመንግስት ልዩ ትኩረት በስፋት የተጀመሩ ስታርት አፖችን በፋይናንስ ለመደገፍ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በፋይናንስ መደገፍ የሚያስችሉ አሠራሮችን በመዘርጋት ወደ ሥራ መግባቱንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሀገራዊ የስታርት አፕ ፖሊሲ ይፋ ከመደረጉ ቀደም ብሎ የሌሎች ሀገራትን ልምዶችና አሠራሮች ሲያጠና መቆየቱንም አስታውሰዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ባንኩ የራሱን የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት አሁን ላይ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

የኦሮሚያ ሕብረት ሥራ ባንክ የኢኖቬሽን ሀብ ዳይሬክተር ገለታ አባተ፤ በተለይም ካለፉት ሁለት ዓመት ጀምሮ ባንኩ ስታርት አፖችን መደገፍ የሚያስችል እንቅስቃሴ እያደረገ ስለመሆኑ ገልፀዋል።

እስከ ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም በሚቆየው አውደ-ርዕይ በመጀመሪያ ደረጃ የምርት ሙከራና ምርት ወደ ገበያ ማቅረብ የጀመሩ ስታርት አፖች በመሳተፍ ላይ ናቸው ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *