



መላው የካፋ ዞን እግር ኳስ ክለቦች ጨዋታ በቦንጋ ሁለገብ ስታዲየም ተጀመረ።
የ2016 ዓ.ም መላው የካፋ ዞን የእግር ኳስ ክለቦች ጨዋታ በቦንጋ ሁለገብ ስታዲየም የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ እና የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ጀምሯል።
የሠላም ተምሳለት፣የአረንጓዴ ፈርጥ እና የክልሉ የፖለቲካና የአስተዳደር መቀመጫ ቦንጋ ከተማ እንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት የቦንጋ ከተማ ከንቲባ አቶ አስማማው አደመ አስተላልፈዋል ።
በከተማችን በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች ስላሉ በቆይታ ጊዜያቸው እንዲጎበኙ ጥሪ ያቀረቡ ከንቲባ የከተማችን አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ተገቢውን አገልግሎት እንደሚሰጡ ሙሉ እምነት አለኝ በማለት ከተማ አስተዳደሩ በሁሉም ነገር ከጎናቸው እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
የእግር ኳስ የክለቦች ጨዋታ ወረዳዎች፣ከተማ አስተዳደሮችንና የተለያዩ ተቋማትን በማቀራረብ የባህል ትውውቅ፣ የልምድ ልውውጥ ፣ የአንድነትና የወዳጅነት ሰሜት በማድረግ የህብረተሰቡን ስፖርታዊ ውድድሮችን ተሳትፎ ለማሳደግ እንደሆነ የካፋ ዞን ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ነፃነት ብርሃኑ ገልጸዋል።
በመላው የካፋ ዞን የእግር ኳስ የክለቦች ሻምፒዮና ላይ 15 ክለቦች መሳተፋቸውን የተናገሩት ኃላፊው በውድድሩ የተሻሉ ተጫዎቾች በማፍራት የዞናችንን እና የክልላችንን እንዲሁም የሀገራችንን ክብርና ዝና የሚያስጠሩ ስፖርተኞችን ለማፍራት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።
ስፖርት ለአካላዊ ብቃትና ለአዕምሮ ጤንነት የጎላ ሚና እንዳለው የተናገሩት የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ በተለይም ለወዳጅነትና የእርስ በእርስ ግንኙነትን ለማጠናከር ትልቅ ቦታ እንዳለው ገልጸዋል።
ስፖርት ትልቅ ታርክ እንዳለ ገልጸው በተለይም እግር ኳስ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳጅነት ያተረፈ እና በኢኮኖሚ ዘርፍ ገቢ ለማመጨት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት እንደሆነም ዋና አስተዳዳሪ ተናግረዋል።
በማስጀመሪያው ፕሮግራም ላይ የጌሻ ወረዳ እና የአዉራዳ ከተማ አስተዳደር የእግር ኳስ ክለቦች በመጫወት ተጀምረዋል ሲል የዘገበዉ የካፋ ዞን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው ።
