




በኢፌዴሪ ሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሰለሞን ሶካ የተመራው ልዑክ በዞኑ የጪዳ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ እንቅሰቃሴዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሰለሞን ሶካ የሚኒስተሩ ዋና ተግባር የወጣቶችን ስብዕና ግንባታ በማሳደግ የተለያዩ አጫጭር ሙያዊ ስልጠናዎችን ወስደው ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀው የጪዳ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ የጀመራቸውን ተግባራትን ማጠናከርና እንደመንግስትና ህዝብ ለዘርፉ መሻሻል ሁለ ዐቀፍ ርብርብ እንደሚሻ አስገንዝበዋል።
የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ በማጠናከር የወጣቶችን ስብዕና ግንባታ ማሳደግና ስራ ዕድል ፈጠራ ማሻሻል እንደሚቻልም ጠቁመዋል።
የሚኒስቴር ቴክኒክና ሙያ ዘርፍ አማካሪ አቶ አዝመራው ከበደ በበኩላቸው የሀገሪቱ ከፍተኛ ሀብት የሆነውን ሰው ማሰልጠንና ማብቃት ከምንም በላይ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን ተናግረው ከወቅቱ ቴክኖሎጂ የሚሄድ ትውልድ መፍጠርና የአከባቢ የሀብት አማራጮች ወደ ገቢ የሚቀየሩበትን ሂደት የማመቻቸት ሙያ ማካበት ይገባል ብለዋል።
የክልሉ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ እንዳሻው ዞናዊ ቅንጅታዊ ስራዎችን በማጠናከር የሚስተዋሉ ችግሮችን መቅረፍ እንደሚገባ አንስተው ኮሌጁ የራስ የውስጥ ገቢ ማሳደግ እንዲችል የተለያዩ አማራጮችን መጠቀም እንደሚገባ በመጠቆም የኮሌጁ ግንባታ ሂደት እንዲጠናቀቅ እንደክልል እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የዞኑ ም/አስተዳዳሪና ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ገዛኸኝ ገዝሙ ኮሌጁ መሠረታዊ ግንባታዎች ባልተጠናቀቀበት ስራ ጀምሮ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ አስረድተው በተለይም አካባቢው የቱሪዝም ኮርደርና በግብርና ዘርፍ እምቅ አቅም ያለው በመሆኑ በቱሪዝምና ሆቴል እንዲሁም አግሮ ፕሮሰስንግና መሠል ዘርፎች ላይ አትኩሮ እንዲሰራ መደረጉን አስረድተዋል።
አሰልጣኞችና ሰልጠኞች በክህሎትና በዕውቀት ብቁ እንዲሆኑ የፌደራልና የክልል መንግስት ድጋፍና ክትትል እንዲጠናከር ጠይቀዋል።
የዞኑ ስራ ክህሎት ኢንተርፕራይዝና ኢንዲስትሪ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሉቃስ በቀለ በበጀት ዓመቱ ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ተመድቦ የተለያዩ ስልጠናዎች የመስጠትና ወደ ስራ የማስገባት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የጪዳ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ለዞኑ ስራ ክህሎት ዘርፍ አስፈላጊ ግብዓት እንዲሆን እየተሰራ እንደሚገኝም አክለዋል።
የኮሌጁ ዲን አቶ ይርጋለም ሚታ ኮሌጁ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በ8 ትምህርትና ስልጠና መስኮች በተለያዩ ደረጃዎች ተማሪዎችን በማሰልጠን ብቁ እያደረጉ እያደረጉ እንደሚገኙ ገልፀው ዘንድሮው 142 ተማሪዎች ተቀብሎ እያስተማረ ይገኛል ብለዋል።
የግንባታው ሂደት በሚገባ ባለመጠናቀቁ ተግዳሮት እየፈጠረባቸው መሆኑን አንስተው ግንባታው እንዲጠናቀቅ፣ ድጋፍና ክትትል እንዲጠናከርና የግብዓት አቅርቦት እንዲደረግላቸው አመልክተዋል።
ልዑኩ በቀጣይም በዞኑ የሚገኙ ሌሎች የልማትና የተፈጥሮ ሀብቶችን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
