ኮርፖሬሽኑ አርሶ አደሩ የግብርና ግብዓት አቅርቦት እንዲያገኝ ለማስቻል ቅርንጫፍ ማዕከላትን እያጠናከረና እያስፋፋ ነው

Spread the love

የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን አርሶ አደሩ የግብርና ግበዓቶችን በአቅራቢያው እንዲያገኝ ለማስቻል ቅርንጫፍ ማዕከላትን እያጠናከረና እያስፋፋ መሆኑን ገለጸ።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ክፍሌ ወልደማሪያም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ካፋ ዞን በኮርፖሬሽኑ ቦንጋ የተቀናጀ የግብርና ግብዓት ሜካናይዜሽን ማዕከል ግንባታና የበቆሎ ዘር ብዜት ማሳን በመስክ ተመልክተዋል።

በዚህ ወቅት አቶ ክፍሌ እንዳሉት፤ ኮርፖሬሽኑ ግብርናውን ለማዘመንና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚረዱ ግበዓቶችን አርሶ አደሩ በአቅራቢያው እንዲያገኝ ቅርንጫፍ ማዕከላትን ለማጠናከር ትኩረት ሰጥቷል።

ያለ ቴክኖሎጂ የሚጠበቀውን ምርታማነት ማረጋገጥ አይቻልም ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ በዚህም ኮርፖሬሽኑ ያሉትን 25 ቅርንጫፍ ማዕከላት የተሟላ ፓኬጅና አገልግሎት እንዲይዙ እየያደረገ ነው ብለዋል።

በተለይም ያሉትን የግብርና ዕምቅ አቅሞችን ለመጠቀም የተቀናጀ የግብርና ግብዓት ሜካናይዜሽን ማዕከላትን የማስፋፋት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ በጀት እየተገነባ የሚገኘው የቦንጋ ቅርንጫፍ ማዕከል የግንባታው ሂደት 60 በመቶ በላይ መድረሱን መመልከታቸውን ጠቁመው፤ በዚህ ዓመት ተጠናቅቆ ወደ አገልግሎት ይገባል ብለዋል።

ማዕከሉ ሲጠናቀቅም በኦሮሚያ ክልል ለጅማ ዞን፣ ጋምቤላ እና ለደቡብ ምዕራብ ህዝቦች ክልሎች የተሟላ አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

የበቆሎ ምርጥ ዘር እጥረት ችግርን ለማቃለል የተጀመረውን ጥረት ለማገዝ በካፋ ዞን ዴቻ ወረዳ በሞዲዮ ንዕስ ጣቢያ እየተከናወነ ያለው የዘር ማብዛት ሂደት በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

በኮርፖሬሽኑ የቦንጋ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ አስረስ አስፋው በበኩላቸው፤ ቅርንጫፉ በክልሉ በተለይም አርሶ አደሩ ግብዓቶችን በአቅራቢያው እንዲያገኝ ያስችላል ብለዋል።

በኮርፖሬሽኑ እየተገነባ የሚገኘው ማዕከል ምርጥ ዘር ማበጠሪያ ማሽኖችንና ሌሎች አገልግሎቶችን አሟልቶ እንደሚይዝ ገልጸዋል።

ይህም ከዚህ ቀደም በአካባቢው የሚመረተው ምርጥ ዘር ወደ ሌላ አካባቢ ሄዶ ተበጥሮ ስለሚመጣ አርሶ አደሩ ላይ የሚያስከትለውን ተጨማሪ ወጪ እንደሚቀንስ ተናግረዋል።

በክልሉ የሚታየውን የዘር አቅርቦት ችግር ለማቃለል ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በራሱና በኮንትራት እርሻ የበቆሎ፣ የሩዝ፣ የቦሎቄ እና ሌሎች ምርጥ ዘሮች እያባዛ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዘንድሮም ከ10 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ነውም ብለዋል።

በቦንጋ ቅርጫፍ የዘር ምርት ባለሙያ አቶ ተካልኝ አርጋው በበኩላቸው፤ በአካባቢው እየተስተዋለ ያለውን የበቆሎ ምርጥ ዘር ችግር ለማቃለል በ23 ሄክታር ማሳ ላይ መነሻ ዘር የማዳቀል ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።

የማዳቀል ስራው ለሁለት ዓመት እንደሚቆይና ጥራቱ ከተረጋገጠ በኋላ ለአርሶ አደሩ እንደሚሰራጭ ጠቁመዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *