




በዳውሮ ዞን በታርጫ ከተማ አስተዳደር በለማት ትሩፋት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነ የከተማው ከንቲባ የሆኑት አቶ ዳዊት ወንድሙ ገልጸዋል ።
የለማት ትሩፋት የስነ ምግብ ስርዓትን ከማሻሻልና ከማጠናከር አልፎ የስራ ዕድልን በመፍጠር ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው የገለጹት የከተማው ከንቲባ ከነዚህም በዶሮ እና እንስሳት እርባታ፣ በጓሮ አትክልትና በበጋ መስኖ የለማ በቆሎና እየለማ ያለው ስንዴ ልማትን ለአብነት አንስተዋል ።
በማህበር ተደራጅተው በወተት አቅርቦት ለከተማው ማህበረሰብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከማበርከትም አልፎ ለወጣቶች ስራ ዕድል በመፍጠር ተሞክሮ ሊሆን የሚችለውን ሻሎም የከብት እርባታ ማህበርን ለአብነት አንስተዋል ።
በመሆኑም ከተማ አስተዳደሩ ከዚህ የተሻለ አቅርቦት በሰፊው በማቅረብ የከተማውን ማህበረሰብ በሰፊው ተጠቃሚ ለማድረግ ከማህበሩ ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ሻሎም የከብት እርባታ ማህበር ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ከፍያለው ከንፈሼ ማህበሩ በመጀመሪያ በአንድ በአካባቢው ላም በቤተሰብ ደረጃ እርባታ የጀመረና በ2013 ወደ ማህበር በማደጉ ከከተማው አስተዳደር ቦታ ተረክበው አንድ የተሻሻለ ዝሪያ ያለውን ላም በመግዛት እርባታ መጀመሩን ገልጸዋል።
በአሁኑ ሰዓት ማህበሩ 10 የተሻሻለ ዝሪያ ያላቸው የወተት ላሞች፣ 4 ግደሮች፣ 4 ኮርማ እና 2 የአካባቢው የምታለቡ ላሞች ፣4 ወይፈንና 4 ግደሮች በአጠቃላይ በድምሩ 28 የወተት እና ለስጋ የሚሆኑ ከብቶችን በማርባት ላይ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም በቀን ከ50 ሊትር በላይ ለከተማ ማህበረሰቡ ከማሰራጨትም በላይ የገቢ ምንጭ ማሳደግ መቻሉን፣ ለ6 ስራ አጦች የስራ ዕድል መፍጠሩን፣ የቤተሰብ ወጪ መሸፈኑን እና በዘር ከ30, 000 ብር በላይ ከወጪ ቀር ገቢ መኖሩን ገልጸዋል።
በቀጣይ በዘርፉ የተሻለ ምርትን በብዛትና በጥራት በማምረት ገበያውን በማረጋጋትና የኑሮ ውድነትን በመግታት ማህበረሰብን ተጠቃሚ ለማድረግ የተሻለ የማምረቻ ቦታ፣ የብድር አቅርቦት እና መብራት እንዲቀርብለት ጠይቋል።
የከተማ ከንቲባው ማህበሩ ሰፋ ያለ የተሻሻለው ዝሪያ ያላቸው ከብቶችን በመግዛት አቅሙን በማሳደግ የኑሮ ውድነትና ገበያውን በማረጋጋት የራሱን ድርሻ እንዲወጣ ችግሩን ለመፍታት የማምረቻ ሼድ ለመገንባት በጨረታ ሂደት ላይ መሆኑን በመግለጽ ሌሎችንም ተራ በተራ ለመፍታት ጥረት እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
በጌታሁን ግርማ
