







የቦንጋ የተቀናጀ የግብርና ግብዓትና የሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከል መገንባት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ለግብርና ስራው መሠረታዊ ችግር የኾነውን የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግር በዘላቂነት የሚፈታ መሆኑ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ግብርናውን ለማዘመን በሰጡት ልዩ ትኩረት ተገንብተው ለአግልግሎት የበቃው ማዕከሉ በአጠቃላይ በክልሉ የግብርና ግብዓት በማሳለጥ እና የግብርና ቴክኖሎጂ በማቅረብ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የጎላ ፋይዳ እንዳለው ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የገለጹት።
ከለውጡ በኃላ የፌዴራል መንግሥት በክልሉ የልማት ፍትሀዊነት ለማረጋገጥ እያደረገ ያለው የልማት እንቅስቃሴ አጅግ አበረታች በመሆኑ ምስጋና ያቀረቡት ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይም ወደ ክልሉ ለሚመጡ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አና የግሉ ዘርፍ አልሚዎች ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።
በምረቃው ስነ-ስርዓት የተገኙት የኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስረከብ የተጀመረው ጊዜ ውጤታማ ስለመሆኑ አንዱ ማረጋገጫ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ የተመዘገበው ከፍተኛ ውጤት መሆኑን ነው ተናግረዋል።
በተለይም ደግሞ ኩታ ገጠም ግብርናን በማስፋፋት፣ የመካናይዜሽን ተደራሽነት በማሳደግ ሁሉንም የግብርና ወቅቶች በአግባቡ ለመጠቀም የተደረገው የተቀናጀ ጥረት በአርሶ አደሩ፣ ከፊል አርብቶ አደሩ እና በዘርፉ በተሰማሩ ባለሃብቶች ዘንድ ከፍተኛ መነቃቃትን ከመፍጠር ባለፈ የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ላለፉት የለውጥ አመታት በአማካይ ከ6% በላይ ዓመታዊ እድገት ማስመዝገብ መቻሉንም እንደዚሁ።
ለዚህ ስኬት ታሪካዊ አሻራቸውን ካኖሩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አንዱ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፥በመላ ሀገሪቱ ግብርናን የማዘመን ግብ አንግቦ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብለዋል፡፡
የመንግሥት የልማት ድርጅቱ ከተቋቋመበት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በውጤታማነት በመዝለቁ በገቢ እና በትርፋማነት ረገድ ከሚሊየን ወደ ቢሊየን በመሸጋገር በ2016 በጀት ዓመት ከ10.7 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ ከታክስ በፊት 1.8 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ትርፍ ማስመዝገብ መቻሉን ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
ኮርፖሬሽኑ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልልን የግብርና ልማት መዳረሻ በማድረግ በካሄደው የተቀናጀ የግብርና ልማት ከክልሉ የእርሻ መሬቶችን በመረከብ ምርጥ ዘር እያባዛ እንደሚገኝ የገለጹት ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ ከዚህ ባሻገር ዛሬ ለምረቃ የበቃውን የቦንጋ የተቀናጀ የግብርና ግብዓት እና የሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከል ገንብቶ ለአገልግሎት ዝግጁ ማድረግ ችሏል ብለዋል።
ሁለገብ ማዕከል ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ብቻ ሳይሆን ለቀጠናው አከባቢዎች ጭምር አገልግሎት እንዲሰጥ ታሳቢ ተደርጎ የተገነባ ዘመናዊ ማዕከል መሆኑን የጠቆሙት ክቡር ሚኒስትሩ የማዕከሉ መቋቋም የምርጥ ዘር፣ የጠጣርና ፈሳሽ የአፈር ማዳበሪያዎች፣ የአግሮኬሚካሎች፣ የእንስሳት መድኃኒት፣ የእርሻ መሣሪያዎች እና መለዋወጫዎች አቅርቦት በስፋት እንደሚኖር እንዲሁም የተቀናጀ የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ እንደሚደረግ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የካፋ ዞንና የቦንጋ ከተማ አስተዳደር ለማዕከሉ ግንባታ መሬት ከማዘጋጀት ጀምሮ ኘሮጀክቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ላደረጋችሁት ድጋፍ ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ የተቀናጀ የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ከመሬት ዝግጅት እስከ ጎተራ የሚዘልቁ የግብርና ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ የገለጹት የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ክፍሌ ወ/ማርያም ከዚህም
ባሻገር ለዘርፉ መዘመንና ለምርትና ምርታማነት እድገት የላቀ አስተዋጽዖ ያላቸውን የግብርና ግብዓቶች እና የእርሻ ተክኖሎጂ ለተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ችሏል፤ እያቀረበም ይገኛል ብለዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ከተቋቋመበት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ አበረታች ውጤት እያስመዘገበ በአዳዲስ ለውጦች ታጅቦ ብቅ ማለቱን የጠቆሙት ስራ አስፈፃሚው ፡የደንበኞችን ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችለውን የISO 9001:2015 የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት እውቅና ማሳካት ከመቻሉም በላይ በኮርፖሬሽኑ የፕሮጀክት ግንባታ ታሪክ በግዙፍነቱ የመጀመሪያ የሆነውን እና 743 ሚሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ የተገነባውን የቦንጋ የተቀናጀ የግብርና ግብዓት እና የሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከል ለማስመረቅ መብቃቱን ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ካለው ጠቀሜታ ባሻገር በአጎራባች ክልሎች እና ዞኖች በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ አርሶ አደሮችን፣ ከፊል አርብቶ አደሮችን፣ የልማት ድርጅቶችን፣ ባለሃብቶችን እንዲሁም የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑንም እንደዚሁ።
በአጠቃላይ ማዕከሉ የክልሉን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ በመጠቀም፣ ግብርናን በማዘመን እና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት የገለጹት አቶ ክፍሌ የማዕከሉ መከፈት ለበርካታ የአካባቢው ወጣቶች ቀጥተኛ እና ተዘዋዋሪ የሥራ ዕድል ይፈጥራልም ብለዋል፡፡
በምረቃው ስነስርዓት የግብርና ሚኒስቴር እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የማህበረሰብ ተወካዮች እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
