










በዞኑ ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ በኢኮኖሚ፣በማህበራዊ፣ በከተማ ልማት እንዲሁም በፖለቲካና ህዝብ ግንኙነት ዘርፎች በልዩ ትኩረት በሚፈፀሙ ተግባራት ዙሪያ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ቀርቦ ውይይት እየተካሄደ ነው።
ውጤታማ ተግባራትን በመፈፀም የህብረተሰቡን እርካታ ለማረጋገጥ ብሎም የዞኑን ልማትና እድገት ለማፋጠን በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ርብርብ ወሳኝ መሆኑም ተጠቁሟል።
ከተማ ልማት፣ግብርና፣ገቢ አሰባሰብ፣ትምህርትና ጤና ዘርፍ ላይ እመርታ ማስመዝገብ ከርብርብ ማዕከላት ዋነኞቹ እንደሆኑም ተገልጿል።
በመድረኩ የተገኙት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ በወቅቱ እንደተናገሩት የዞኑን ልማትና እድገት ለማፋጠን በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ርብርብ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ለዞኑ ልማትና እድገት እንዲሁም ለህብረተሰቡ ኑሮ መሻሻል የአመራሩ በተግባርና በአስተሳሰብ አንድ መሆን ሚናው የጎላ ነው ሲሉም ጠቁመዋል አቶ አልማው።
በዞኑ ሠላምን ለማረጋገጥ የተሠራው ስራ በልማትም ሊደገም እንደሚገባ የጠቆሙት አቶ አልማው የሠላምና ፀጥታ ስራ የሁልጊዜም የርብርብ ማዕከላችን ነውም ብለዋል።
የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ በበኩላቸው
በዋና ዋና የንቅናቄ አጀንዳዎች የተሻለ ዉጤት ለማምጣት ጠንክሮ፣ተግባብቶና ተናቦ መስራት ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ በአፅንኦት አንስተዋል።
በዞኑ በሁሉም ዘርፍ የተመዘገበው ውጤትም ሆነ የታየው ክፍተት ድምር ውጤቱ አመራሩ የመራበትንና ያስተባበረበትን ያሳያል ብለዋል።
በቀረበው ዕቅድ መነሻ ከ2017 በጀት ዓመት ጀምሮ በዋና ዋና ዘርፎች የተሻለ ዉጤት በዞኑ ለማስመዝገብ ቀን ከሌት መትጋት እንደሚጠበቅ ገልፀዋል አቶ አበበ።
በዞኑ ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ በሚከናወኑ ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረ ዕቅድ በአካባቢው ተወላጅ ምሁራንና አመራሮች ቀርቧል።
በመድረኩ የአካባቢ ተወላጅ የክልል አመራሮች፣የዞን አጠቃላይ አመራሮች እና የወረዳና/የከተማ አስተባባሪዎች እንዲሁም በተለያዩ አካባቢ የሚገኙ የዞኑ ተወላጅ ምሁራን እየተሳተፉ ይገኛሉ ሲል የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዘግቧል።
