








የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢ ጉዳዮች ቢሮ የምግብና ስርዓተ ምግብ ደህንነት ፕሮጀክት(BREFONS) የአየር ንብረት ለውጥን በፖሊሲዎች፣ እቅዶች እና ፕሮጀክቶች ውስጥ ለማካተት ለባለድርሻ አካላት ግንዛቤ ለመፍጠር የተዘጋጀ የስልጠና መድረክ በሚዛን አማን አካሂዷል፡፡
በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ መሠረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋጂዮ ሳፒ በሁሉም አካባቢዎች የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን ለመቋቋም ባለድርሻ አካላት ከዕቅዶቻቸውና ከፕሮግራሞቻቸው ጋር አስተሳስረው መስራት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡
በክልሉ የአየር ንብረት ለውጥ ችግሮችን ለመቋቋም በፕሮጀክቶች የሚደረጉ ድጋፎችን በተገቢው መጠቀምና ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግም ገልፀዋል፡፡
የክልሉ አርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ታምሩ ቦኒ በበኩላቸው የአየር ንብረት ለውጥ ዓለማችንና ለሀገራችን አስቸጋሪ እና ፈታኝ ከሆኑ ሁኔታዎች አንዱ መሆኑን ጠቁመው ችግሩን በመቅረፍና በመፍታት እንደ ክልል ልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በቆላማው አካባቢ የሚኖሩ አርሶና አርብቶ አደር ማህበረሰብ በአየር ንብረት ለውጥን የሚመጡ ችግሮችን በዘላቂነት መቋቋም እንዲችሉ ዘላቂ መፍትሔ ተብለው የታለዩ መንገዶችን መከተል እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡
ስልጠና ዋና ዓላማው በአርብቶ አደርና ከፍል አርብቶ አደር ማህበረሰብ አካባቢ የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋምና በመለማመድ በችግሩ ሊከሰቱ የሚችሉ የድርቅ አደጋ እንዲከላከለው ማድረግ መሆኑን የምግብና ስርዓተ ምግብ ደህንነት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ኦይጌሌች ገልፀዋል፡፡
በክልሉ 8 ወረደዎች ውስጥ የሚገኙ በ40 ቀበሌዎች የሚገኙ 454,084 የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ተስፋዬ ፕሮጀክቱ በሚሰረባቸው አካባቢ የሚገኙ ማህበረሰብ የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም ምርትና ምርታመናቱን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ በአርብቶ እና ከፍል አርብቶአደር ማህበረሰብ ኑሮ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ ለዚህም የውሃ መሠረተ ልማት ግንባታ፣ የእንስሳት ሀብት ጥበቃ፣ የመሬት ሀብት ዘርፍ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አቶ ተስፋዬ ኦይጌሌች አብራርተዋል፡፡
በቀጣይም 1750 ሄክታር በላይ መሬት በአርብቶ እና ከፍል አርብቶአደር ማህበረሰብ አከባቢ ተጠብቆ ምርትና ምርታማነቱ የሚያሰድግበት ሁኔታ ለመከታተል መታቀዱን ገልፀዋል፡፡
ኘሮጀክቱ የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም የአርብቶ አደሩንና ከፍል አደሩን ማህበረሰብ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግና የአኗኗር ዘይቤን በማሻሻልና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጠ ውጤታማ ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን የተገለፀ ሲሆን በቀረቡት 7 የስልጠና ሰነዶች ዙሪያ ከተሳታፊዎች የተነሱ ጥያቄዎችንና አስተያየቶች ላይ ከመድረኩ ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት የስልጠና መድረክ ተቋጭቷል።
በተከተል ወ/ሚካኤል
