በኢኮኖሚ ፣በፖለቲካና በማህበራዊ ዘርፎች የሚስተዋሉ ጉድለቶችን በማረም የተሻለ ውጤት ለማስመዘገብ አመራሩ ቁርጠኛ ሆኖ ሊሰራ እንደሚገባ የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ አሳሰቡ::

Spread the love

የካፋ ዞን ወቅታዊ የፓርቲና የመንግስት ሥራዎችን አፈጻጸም በመገምገም የቀጠይ ትኩረት አቅጣጫ ላይ ትኩረት ያደረገ የውይይትና የምክክር መድረክ አካሂዷል።

የካፋ ዞን የብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት የመንግስት ረዳት ተጠሪና የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊው አቶ ታከለ ታምሩ ወቅታዊ የፓርቲና የመንግስት ተግባራት አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል ፡፡

ከነዚህም መካከል የፓርቲ የተለያዩ አደረጃጀቶች፣ የአመራር እና የአባላት ሁኔታ፤ ከመንግስት ሥራዎች አኳያ የግብርና ምርትና ምርታማነት መጨመር፤ የሌማት ትሩፋት ፤ የመስኖና የቡና ልማት፤የፍራፍሬ ልማት፤ የእንተርፕራይዝና የሥራ ዕድል ፈጠራ፤ የንግድና እንቨስትመንት እንቅስቃሴ፤ የኮሪደር ልማት ሥራዎች፤ የገቢ አሰባሰብ ውጤታማነት፤ የመንገድና ሌሎች መሰረተ ልማቶች፤ የሴቶችና የወጣቶች ተሳትፎ፤ የትምህርትና የጤና ልማት ሥራዎች በዋናነት ውይይትና ምክክር ከተደረገባቸው ጉዳዮች መካከል ናቸው።

ሪፖርቱን መነሻ በማድረግ የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ በኢኮኖሚ ፣በፖለቲካና በማህበራዊ ዘርፎች የሚስተዋሉ ጉድለቶችን በማረም የተሻለ ውጤት ለማስመዘገብ አመራሩ ቁርጠኛ ሆኖ ሊሰራ እንደሚገባና ይህንን ታሳቢ ያደረጉ ሀሣቦች መነሳት እንዳለባቸው አቅጣጫ አስቀምጠዋል ፡፡

የመድረኩ ተሣታፊ አመራሮች በሰጡት አስተያየት የተቀመጠውን አቅጣጫ ተከትሎ በቁርጠኝነት፣ በተነሳሽነትና በቁጭት በመስራት ውጤት እንደሚያስመዘግቡ ተናግረው ከአቅም በላይ የሆኑ የመሰረተ ልማትና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች በዞን፣ በክልልና በፌዴራል መንግስት በተገቢው ተይዘው መሰራት አለባቸው ብሏል።

በመንገድ መሠረተ ልማት፣ በጤናና በትምህርት ፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና በሌሎችም የሚስተዋሉ ጉድለቶችን በማረም አበረታች ውጤት ለማምጣት ተቀናጅቶ እንደሚሰሩ የጋራ ስምምነት ላይ ተደርሰዋል ፡

አቅዶ መሥራት ፣የተጠናከረ አደረጃጀት መፍጠር፣ በአመለካከትና በተግባር አንድነት መፍጠር እና የመረጃ ሥርዓት ለማዘመን ልዩ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባም በመድረኩ ተመላክቷል ፡፡

የህግ የበላይነት ማስከበር፤ ህገ-ወጥ የነዳጅና የሌሎች ምርቶች የዋጋ ጭማሪ መከላከል ጋር በተያያዘ የአመራሩ ቁርጠኝነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ሊሆን እንደሚገባም ተገልጸዋል።

በመጨረሻም የካፋ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪና የብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊው አቶ አጥናፉ ኃይሌ በቀጣይ ለወረዳና ከተማ አስተዳደር አጠቃላይ አመራሮች የሚሰጠውን ሥልጠና ጨምሮ ሌሎች ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ የሥራ መመሪያና አቅጣጫ ሰጥቷል።

በመድረኩ የዞን አጠቃላይ አመራሮች፤ የወረዳና ከተማ አስተዳደር አስተባባሪዎች እና የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ተሳትፈዋል ሲል የዘገበው የካፋ ዞን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *