በሁለቱ ክልል አጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮችን ለመፍታትና ዘላቂ ሠላምን ለማስፈን አመራሩ በቅንጅት መስራት እንዳለበት ተጠቆመ

Spread the love

በጋምቤላ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ባሉት አጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮች ዙሪያ የውይይት መድረክ በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ ተካሂዷል።

በሁለቱ ክልሎች የሚገኙ አጎራባች ዞኖች እና ወረዳዎች አልፎ አልፎ የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮችን ለመፍታትና ዘላቂ ሰላምን ለማፅናት የተዘጋጀ መነሻ ዕቅድ ቀርቦ በስፋት ውይይት ተደርጓል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አለሙ ከዚህ ቀደም የነበረው የፀጥታ ችግር በተሰራው ስራ ሠላም መስፈኑን ጠቁመው በመዋቅሮች ላይ የሚስተዋሉ የሽፍታ እንቅስቃሴዎችና ህገወጥነትን ለመግታት የፀጥታ መዋቅር አመራር በልዩ ሁኔታ በመገምገም መፍታት እንደሚገባው ተናግረዋል።

ለህዝቦች አብሮነትና አንድነት መጠናከር ፣ሠላማዊ የሆነ ቀጠና እንዲፈጠር ፣የማህበረሰቡ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ እና የህዝቦች አብሮነት እንዲጠናከር መስራት እንደሚገባ አክለው ገልፀዋል።

በመቀናጀት ህገ ወጥነትን መከላከል ይቻላል ያሉት የጋምቤላ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ከሎ ባንግ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ የአመራር አንድነትና መተማመንን በማስፋት ችግሮችን መፍታት እንደሚቻል ተናግረዋል።

በመንግስትና በህዝብ መካከል መልካም ግንኙነትና የመረጃ ልውውጥ እንድኖር የህዝቦች አብሮነትና ትስስር እንዲጠናከር እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ መስራት ይገባናል ብለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮችን ለመፍታትና ዘላቂ ሰላምን ለማፅናት የአመራሩን ቅንጅትና ትብብርን የሚጠይቅ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ በተወሰኑ ወረዳዎች ላይ የሚስተዋሉ የወሰን ማስከበር፣ዘረፋና ህገ ወጥ ንግድ፣የሽፍታ እንቅስቃሴዎች እና ሌሎች የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ጊዜ ሳይሰጡ በመፍታት ወደ ልማት ስራዎች መግባት ይገባናል ብለዋል።

በውይይት መድረኩ የሁለቱ ክልሎች የፀጥታ መዋቅር አመራሮች ፣የቤንች ሸኮ የማጃንግና የሸካ ዞን አመራሮች ፣የፀጥታ መዋቅር አመራሮችና የፖሊስ አዛዦች ፣ የየኪ ወረዳ፣የሸኮ እና የጉራፈርዳ ወረዳ አመራሮች ተገኝተዋል ሲል የሸካ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *