የአፍሪካ ልማት ባንክ የኢትዮጵያን የለውጥ አጀንዳ እንደሚደግፍ ገለጸ

Spread the love

የአፍሪካ ልማት ባንክ የኢትዮጵያን የለውጥ አጀንዳ በበጀት ጭምር እንደሚደግፍ የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ ፕሬዚዳንት ሲዲ ኦልድ ታህ(ዶ/ር) ገለጹ።

የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ከአዲሱ የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ ፕሬዚዳንት ሲዲ ኦልድ ታህ(ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል።

የዓለም ባንክ እና አይ ኤም ኤፍ አመታዊ ስብሰባዎች ጎን ለጎን ነው የሁለትዮሽ ትብብርን ለማጠናከር ሁለቱ ወገኖች ውይይቱን ያደረጉት።

አቶ አህመድ ሺዴ በኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ እና የኢንቨስትመንት አካባቢን ምቹ የማድረግ ፣ ቁልፍ በሆኑ ዘርፎች ምርታማነትን የማሳደግ እና የመንግስት የአገልግሎት አሰጣጥ አቅምን ለማጠናከር ያለሙ የሪፎርም ስራዎችን አስመልክተው ለፕሬዚዳንቱ ገለፃ አድርገዋል።

በአዲሱ ግዙፍ የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ፕሮጀክት ላይ አዳዲስ መረጃዎችን ያካተተ ውይይት ያካሄዱ ሲሆን የአፍሪካ ልማት ባንክ ፋይናንስ በመስጠት ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አስረድተዋል።

ሲዲ ታህ የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ ፕሬዚዳንት ሆነው በመመረጣቸው የእንኳን ደስ ያለዎት ያሉ ሲሆን በአመራር ሰጭነታቸው ሙሉ እምነት እንዳላቸው ገልፀው፣ ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ጋብዘዋል።

ፕሬዚዳንት ሲዲ ኦልድ ታህ(ዶ/ር) በበኩላቸው የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ እና የሪፎርም አጀንዳዎች አፈፃፀም አድንቀዋል።

ባንኩ የሀገሪቱን ትልቅ የለውጥ አጀንዳ በበጀት ድጋፍ፣ በግብርና እና በመሰረተ ልማት ላይ ኢንቨስት በማድረግ በተለይም የአየር ትራንስፖርት ትስስርን በማጠናከር የቀጣናዊ ትስስርና ውህደት እንቅስቃሴዎች ላይ ድጋፍ ለማድረግ ያለውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል።(ኤፍ ኤም ሲ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *