











በክልሉ የሰንበት ገበያዎችን በማቋቋም የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው
መንግስት የኑሮ ዉድነትን ለማረጋጋት አዳዲስ መመሪያ በማዘጋጀትና የተለያዩ ፖሊሲዎችን በመቅረጽ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል።
በዚህም የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት የማሕበረሰቡን ኑሮ ጫና ማቃለል እንዲያስችል የሰንበት ገበያዎች ተቋቁመው ማሕበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሰራ ነው።
ሰንበት ገበያው የተለያዩ መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን ከአምራቾች ወደ ሸማቹ ቀጥታ በማድረስ የዋጋ ጭማሪን ለመቆጣጠር ያግዛል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በ2018 በጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት የሰንበት ገበያ ማጠናከር ይረዳ ዘንድ 3 ሚሊዮን 845 ሺህ ብር ተመድበው ሥራዎች ሲሰሩ መቆየቱን የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታውቀዋል።
የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትልና የገበያ ልማት ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ አሰገደች ወልደዬ፤ ሰንበት ገበያ በንግድ ስርዓቱ ያለውን ሰንሰለት በማሳጠር አምራቹን ከሸማቹ ጋር በቀጥታ በማገናኘት ኑሮ ውድነት እንዲረጋጋ የሚጫወተው ሚና የላቀ ነው ብለዋል።
እንዲሁም አምራቹ ያለማንም ከልካይነት በነፃ ምርቱን ወደ ገበያ በማቅረብ በገበያዎች እሴትን ሳይጨምሩ የኑሮ ውድነት የሚያባብሱ ደላሎችን በማስወጣት በተመጣጣኝ ዋጋ ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለሸማቹ እንዲያቀርብ እንደሚያስችል ነው ወ/ሮ አሰገደች ወልደየስ የተናገሩት።
ሰንበት ገበያ መቋቋም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ከመደበኛ ገበያ በተለየ ሁኔታ ማህበራትና በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያቀርቡ የጅምላ ነጋዴዎች ቀጥታ ከአምራች ምርት እንዲያገኙ በማድረግ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደርጋልም ብለዋል።
በክልሉ የሰንበት ገበያን ተግባር ወደ መሬት ለማዉረድ በዝግጅት ምዕራፍ ወቅት ከሁሉም ዞንና ከተማ አስተዳደር መዋቅሮች ጋር ሰነድ በማዘጋጀት የመግባቢያ መድረክ በመፍጠር ወደ ተግባር መገባቱንም የተናገሩት ኃላፊዋ፤ ለስኬታማነቱ በየደረጃው ድጋፍና ክትትል በተጠናከረ መልኩ ተከናውነዋል ነው ያሉት።
በክልሉ በበጀት ዓመቱ ባለፉት ስድስት ወራት ዘጠኝ ነባር ሰንበት ገበያዎችን ማጠናከር፣ ስምንት አዲስ የሰንበት ገበያ ከመክፈት በተጨማሪ 19 የምሽት ገበያዎች መክፈት መቻሉንም ተናግረዋል።
እነዚህን ሰንበት ገበያዎችን ማጠናከር እንዲያስችል 3ሚሊዮን 845 ሺህ ብር ተመድበው ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውንም ወ/ሮ አሰገደች ወልደየስ አስረድተዋል።
በሰንበት ገበያዎች የፍጆታ እቃዎች በተለይም ዘይት፣ስኳር፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣እንቁላል፣የንፅህና መጠበቂያ እና ሌሎች
ምርቶችን ህብረት ስራ ማህበራትና በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያቀርቡ የጅምላ ነጋዴዎችን በማግባባት ምርቶችን ከአምራች ቀጥታ እየገዙ እንዲያቀርቡ በማድረግ የገበያ ትስስር መፍጠር ተችሏል ብለዋል።
በዚህም ከመደበኛ ገበያዎች በሊትር/በኪ.ግ ከ10-30 ብር ልዩነት በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችና የከተማዉ ማህበረሰብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት።
በቀጣይነት በየመዋቅሩ የሰንበት ገበያ ያልተቋቋመባቸዉ ከተሞች ላይ እንዲቋቋም ድጋፍና ክትትል እየተደረገ ይገኛልም ብለዋል ኃላፊዋ።
በተጨማሪም የግብርናና ሌሎች የኢንዱስትሪ ምርቶች በሁሉም የሰንበት ገበያዎች በተመጣጣኝና በተከታታይ እንዲቀርብ ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራና በተቀናጀ እንደሚሰራም ገልጸዋል ወ/ሮ አሰገደች ወልደዬስ ።
በፍቅር ከበደ
