




“የታደሰ ጂኦስትራቴጂያዊ ቁመና በሁሉም ኢትዮጵያዊያን የጋራ ትጋት” በሚል መሪ ቃል በሸካ ዞን በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ አጠቃላይ የዞን ማዕከል መንግስት ሠራተኞች ውይይት በቴፒ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የሸካ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለማየሁ አለሙ እንደገለጹት የመድረኩ ዓላማ ዓለም ዓቀፋዊ፣ አህጉራዊና ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን መሠረት በማድረግ፣ የታደሰ ጂኦስትራቴጂያዊ ቁመና በሁሉም ኢትዮጵያዊያን የጋራ ትጋት እንዲረጋገጥ የጋራ መግባባትና አረዳድ ለመፍጠር ነው ሲሉ ጠቁመዋል።
አቶ አለማየሁ አክለውም ሀገርን ከጂኦ-ስትራቴጂያዊ ኩስመና ወደ ታደሰ ቁመና የማሸጋገር ሂደት ውስጥ ብሔራዊ ጥቅምን ከማስከበር አኳያ የመንግስት ሠራተኛው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ ለማፋጠን የተመዘገቡ ድሎችን ማስቀጠል እና ብሔራዊ ጥቅሞቻችንንና ድሎቻችንን ለማፅናት በአንድነት መቆም እንደሚገባ ገልጸዋል።
ለመወያያ የተዘጋጀ ሠነድ በሸካ ዞን ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ተግባሩ እንደሻው እና በዞኑ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ሸሎ አዴሎ እየቀረበ የሚገኝ ሲሆን በሠነዱ መነሻ ሰፊ ውይይት ይካሄዳል ተብሎም ይጠበቃል።
በመድረኩ የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ፣የሸካ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለማየሁ አለሙ፣የሸካ ዞን ምክር ቤት ዋና አፌጉባኤ የተከበሩ አቶ ዮሐንስ ካሳሁንን ጨምሮ የሸካ ዞን አጠቃላይ አመራሮችና የመንግስት ሠራተኞች እየተሳተፉ ይገኛሉ ሲል የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።
