



በጤና ተቋማት ለእናቶች የሚሰጡ አገልግሎቶችን በማዘመን በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ ዜጎችን ህይወት ለመታደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።
የጤናማ እናትነት ወር ”ጥራቱን የጠበቀ የምጥ እና የወሊድ እንክብካቤ ለሁሉም እናት፤ ለጤናማ እናቶች” በሚል መሪ ሀሳብ መከበር ጀምሯል።
የጤናማ እናትነት ወር በአለም አቀፍ ደረጃ ለ38ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ19ኛ ጊዜ እየተከበረ ነው።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ ዛሬ በጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል መርሃ ግብሩ በተጀመረበት ወቅት እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ በወሊድ ምክንያት የሚመጣ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ በርካታ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል።
በአሁኑ ወቅትም ለእናቶች የሚሰጠውን የሕክምና አገልግሎት በማዘመን በወሊድ ምክንያት የሚመጣን የእናቶች ሞት ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በሀገሪቱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2030 በዘርፉ ለማሳካት የታቀደውን ግብ ከማሳካት አንፃር ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።
ከእርግዝና በፊት፣ በእርግዝና ወቅትና በወሊድ ወቅት በሚደረጉ ክትትሎች የእናቶችን ጤና ለማስጠበቅ መሆኑን ገልጸው፤ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
ከተግባራቱ መካከል ወደ ተቋማት የሚመጡ እናቶችን ቁጥር ከመጨመር ባለፈ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ አንዱ እንደሆነ ተናግረዋል።
በዋናነትም የመጀመሪያ ደረጃ የጤና እንክብካቤ በሁሉም ተቋማት እንዲሰጥና ነፍሰጡር እናቶች ያሉበት ስፍራ ላይ አገልግሎቱ በቅርበት እንዲሰጥ እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።
የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ በበኩላቸው፤ አስቀድሞ መከላክል በሚቻሉ በሽታዎች የእናቶች ሞት እንዳይከሰት ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
ለዚህም መንግስት የእናቶችና ሕፃናት ጤና አገልግሎት በነፃ እንዲሰጥ ከማድረግ በተጨማሪ ተቋማቱ በሰው ሃይልና በቁሳቁስ የተሟሉ በማድረግ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ወደ ጤና ተቋማት የሚመጡ እናቶች ምቾት እንዲሰማቸው ከማድረግ አንፃር በርካታ ስራዎች የተከናወኑ ቢሆንም አገልግሎቱ በሚፈለገው ደረጃ እርካታ እንዲመጣ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ከእርግዝና እና ከወሊድ ጋር በተያያዘ የእናቶችና የጨቅላ ሕፃናትን ሞት የመቀነስ ተግባር ውጤታማ ከሚያደርጉ ተግባራት መካከል ያለ እቅድ የሚከሰት እርግዝና ተጠቃሽ መሆኑንና ለዚህም ውጤታማና ዘመናዊ የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴዎችን መጠቀም ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለአንድ ወር በሚካሔደው የእናትነት ወር ላይ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሮች እንደሚከናወኑም ጠቅሰዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
