
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ በክልሉ ያሉ ከተሞችን ውብ፣ ጽዱና ለዜጎች ምቹ ከማድረግ አንጻር ዘርፌ ብዙ ተግባራትን ያከናውናል።
ከነዚህም አንዱ በቢሮው የመሬት ልማት ማኔጅመንት ዘርፍ የሚሰሩ ስራዎች ናቸው። ዘርፉ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል በዋናነት ለአልሚዎች ጥራት ያለውንና ለተለያዩ አገልግሎት የሚሆን መሬትን በበቂ ሁኔታ ማዘጋጀት፣ የተዘጋጀውን መሬት በተቀመጠው አሠራር ስርዓት አዋጅና ደንብ መሠረት ማስተላለፍ፣ መሬትን በአግባቡ ማስተዳደር ናቸው።
ከላይ የተገለጹ ሦስት ዋና ዋና ተግባራትን ዕውን ለማድረግ ተቋሙ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ም/ኃላፊና የከተሞች መሬት ልማት ማኔጅመንት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጫናቸው ወንድሙ ገልጸዋል።
በዚህ መሠረት መሬትን ለአልሚዎች፣ መኖሪያ ቤት ግንባታና ለተለያዩ አገልግሎት ከማዘጋጀት በ2017 ዓ/ም 980 ሄክታር ለማዘጋጀት ታቅዶ 915 ሄክታር ማዘጋጀት መቻሉን አቶ ጫናቸው ገልጸዋል።
የተዘጋጀውን መሬት ከማስተላለፍ/ትልልፍ 800 ሄክታር ታቅዶ 855 ሄክታር በጨረታና በምደባ ማስተላለፍ መቻሉን ተናግረዋል።
በሦስተኛ ደረጃ ከቅረታ ነፃ በማድረግ መሬትን በአግባቡ ከማስተዳደር አንጻር ሰፋ ችግሮች የነበሩበት በመሆኑ ችግሮቹን ለመፍታት በርካታ ተግባራት መከናወናቸውንም አቶ ጫናቸው አክሏል።
ከሚታዩ ችግሮች ዋና ዋናዎቹ የህገወጥ መሬት ይዞታዎችና ግንባታ መበራከት፣ ሰነድ አልባ ይዞታዎች፣ በአመለካከት ይዞታው የግሌ የቤተሰብ ውርስ በመሆኑ ሰነድ አያስፈልገኝም ማለት፣ በትርፍነት የተያዙ/በማስፋፋት የተያዙ ይዞታዎች እንዲሁም በከተሞች በማስፋፊያ አካባቢዎች ያሉ የአርሶ አደሮች ይዞታ ያለመመዝገብ እንደሆኑ አብራርተዋል።
እነዚህን ችግሮች ከመሠረቱ ለመፍታትና መሬትን በአግባቡ ለማስተዳደር የደንብ ቁጥር 12/2015 በክልል ደረጃ መዘጋጀት እና ለማስፈጸሚያነት በቢሮው የአፈጻጸም መመሪያ 1/2015 የህግ ማዕቀፍን በማዘጋጀት ወደ ስራ መገባቱን የቢሮ ም/ኃላፊው ተናግረዋል።
በተዘጋጀው ደንብና መመሪያ መሠረት በስድስቱ ዞኖች 32,682 ህገወጥ ይዞታዎች ከተመዘገቡት መካከል የማጣራት ስራ ተሰርቶ የተለዩት 27,526 ይዞታዎች ማረጋገጫ መሰጠቱን ተናግረዋል።
በከተሞች ፕላን ማስጠበቅና የይዞታ ማረጋገጥ አንጻር ቀሪዎቹን ወደ 3ሺ የሚጠጉት ተለዋጭ ይዞታ ከሚፈልጉት መካከል 1200 ያህሉን በቦታው በማሸጋሸግ ተለዋጭ ይዞታ የተሰጣቸው ሲሆን ቀሪዎቹ በአሰራሩ መሠረት ተለዋጭ ይዞታዎችን ለማዘጋጀት በተዋረድ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
ከላይ የተጠቀሱ ይዞታዎችን ወደ ህጋዊ አሠራር ውስጥ ማስገባት መቻሉ ለከተሞች ዕድገትና ለዜጎች ጥያቄዎችን ከመመለስም ባሻገር ዘርፌ ብዙ ፋይዳዎችን ማበርከቱ መቻሉን የቢሮ ም/ኃላፊው ገልጸዋል።
ለከተማው ነዋሪዎች ከኢኮኖሚ አንጻር የይዞታ/የንብረት ባለቤትነትን በመረጋገጡ በዋስትና ማስያዝ፣ ብድር መውሰድና ሌሎች ጥቅሞችን ማስከበር መቻሉን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ከተሞችን በማነቃቃት ወደ ለውጥ ማስገባት፣ መሠረተ ልማትን ለማሟላት የተለያዩ ህብተሰብ ክፍሎችን በማገናኘት፣ የመሬት ጥቅምን ከፍ ማድረጉ፤ የተለያዩ የከተሞች አካባቢ የተዘረጉ የፓርትና የመንግስት ኢንሼቲቮችን ዕውን ለማድረግ እንዳገዛቸው አንስተዋል።
ከገጠር ወደ ከተማ ሲገቡ ያልተመዘገቡ ነገር ግን ግብር የሚከፍሉ ቤት ገንብቶ እየኖሩ ያሉ 5000 ሰነድ አልባ ይዞታዎች ለመመዝገብ ታቅዶ 4535 ማከናወን መቻሉ አፈጻጸሙ 90% መሆኑን ገልጸዋል።
በከተሞች ማስፋፊያ አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮችን ጊዜያዊ የመጠቀሚያ ሰርተፒከት ማዘጋጀትና ከመስጠት አንጻር 8ሺ ከታቀደው 4524 ሰርተፍኬት በ112 ከተሞች/ማዘጋጃ ቤት ባለባቸው መስጠት መቻሉን ተናግረዋል።
በከተሞች በመስፋፋት የተያዘ ይዞታዎች ወደ ህጋዊ መስመር ከማስገባት 1600 የመለየት ስራ መሰራት መቻሉም አንስተዋል።
ለተግባራቱ ስኬታማነት የባለድርሻ አካላት ቅንጅት እስከታችኛው ማዘጋጃ ቤት ድረስ እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ ተቋማት በመደጋገፍና በመናበብ እየተሰራ መቆነቱን ጨምረው ገልጸዋል።
መንግስት በየጊዜው የሚያወጣቸውን አዋጅና ደንቦችን መፍራት/መጠራጠር ፣ በሂደቱ ላይ በአመራርና ባለሙያዎች ዘንድ የስነምግባርና የዲስፕሊን ችግሮች መታየት፣ ተዘጋጅቶ የተላለፈውን ይዞታዎችን አለማልማት/አጥሮ ማስቀመጥ፣ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚሆን በቂ መሬትን ከማዘጋጀት ውስንነት መታየቱን እንደ ተግዳሮት ጠቅሰዋል።
ሰነድ አልባ ይዞታዎችን ማጽዳትና ማጠናቀቅ፣ በማስፋፋት የተያዙ ይዞታዎችን መስመር ማስያዝና ጊዜያዊ መጠቀሚያ ሰርተፒከት ማዘጋጀት፣ የመሬት ሀብት ቆጠራ ምዝገባ በሰፊው ማቅረብ የቀጣይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በመሆኑም ውስን የሆነውንና በከተሞች የሀብት ሁሉ ምንጭ የሆነውን የከተማ መሬት የባለድርሻ አካላት በህግና በደንቡ መሠረት በመለየት፣ ህጋዊ አሠራር ውስጥ በማስገባትና በመምራት ወደ ሀብት ማመንጫ መቀየር እንደሚገባ በአጽንኦት ተናግረዋል።
በመጨረሻም ሰነድ አልባ ይዞታዎች፣ በመስፋፋት የተያዙ ይዞታዎችን ህጋዊ ከማድረግ እንዲሁም ለአርሶ አደሮቹ ጊዜያዊ መጠቀሚያ ሰርተፍኬት መስጠት የቀጣይ የዕቅዱ የትኩረት መስኮች በመሆናቸው የባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ማንኛውም በከተማ የተካለለ ይዞታ ባለቤትነቱ እንዲረጋገጥ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አሳስበዋል።
