




በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግሥት የብዝሀ ሴክተር የምግብ ሥርዓትና የሥርዓተ ምግብ ፕሮግራም የምግብ ሥርዓት ሥልጠና እና የዞን የምግብ ሥርዓት እና ኒዩትሪሽን ምክርቤት ማጠናከሪያ እና ማነቃቂያ መድረክ በሚዛን አማን ከተማ ተካሂዷል።
የምግብ ስርዓት እና ኒውትርሽን ምክር ቤት በዞንና ወረዳ ደረጃ ማቋቋም፣ የስርዓተ ምግብ ተግባራትን እስከ ቀበለ ማሳወቅና ማነቃነቅ እንዲሁም የስራዓተ ምግብ መረጃ አደረጃጀት እና ክትትል ላይ ያተኮረ ሰነድ በዘርፉ ባለሙያዎች አቅርበው ዉይይት ተደርጓል።
በመድረኩ የክልሉ የምግብ ስርዓትና ሥርዓተ ምግብ ማስተባበሪያ ዩኒቲ አስተባባሪ አቶ ማቴዎስ ማልዳዬ እንደተናገሩት ፤ በክልሉ የምግብ ስርዓት እና ስርዓተ ምግብ አመጋገብ ዘይቤን በመቀየር የግብርና ምርቶችን በስፋት በማምረትና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
በትንሽ ማሳ የተለያየ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ስራስር እና የአዝርዕት ምርቶችን እና በአካባቢያችን በቀላሉ ማግኘት የሚንችላቸው ምርቶችን በማምረት እንዲሁም የእንስሳት ምርት አጠቃቀም በማሳደግ በስብጥር መመገብ ይጠበቃል ነው ያሉት።
በዚህም የህጻናት መክሳትና መቀንጨርን እንዲሁም ከምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ የጤና ችግሮችን መከላከል፣ የአጥብ እና ነፍሰጡር እናቶች አመጋገብ ሥርዓት በማሻሻል በጽንስ ውስጥ የሚፈጠረው መቀንጨርን ለመቀነስ በክልል ደረጃ የተጀመሩ ተግባራትን ለማጠናከር በትኩረት ይሰራልም ብለዋል።
በክልሉ የምግብ ስርዓትና ስርዓተ ምግብን ውጤታማ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት እንዲጠናከሩ ቁልፍ ባለድርሻዎች ሚናቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
የተጀመሩ አሠራር ኢንሼቲቮችን ውጤታማ ማድረግ እንዲቻል የብዙሃ ሴክተር ቁልፍ ባለድርሻዎች ትብብርና ቅንጅት ለዘርፉ መሻሻል የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነውም ብለዋል።
በዚህም የዞንና የወረዳ መዋቀር ቁልፍ ባለድርሻዎች ለዘርፉ ልዩ ትኩረትና ክትትል በመስጠት በየደረጃው ተግባራትን ቆጥሮ የሚያከናውን እና በባለቤትነት የሚመራ የስራዓተ ምግብ ምክር ቤት ተቋቁሞ ሊሰራ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥቷል።
በቀበሌ ደረጃም ጭምር የስራዓተ ምግብ ቴክኒክ ኮሚቴዎችን ማቋቋምና ተግባራትን ለህብረተሰቡ ጠቃሚ በሚሆን መልኩ በማከናወን ረገድ የብዝሃ ሴክተር ምግበ ሥርዓት እና ኒዩትሪሽን ምክርቤት ቤቶች በትኩረት መስራት አለባቸውም ብለዋል አቶ ማቴዎስ ማልዳዬ።
አስተባባሪው በማከልም የስርዓተ ምግብ መረጃ ቋት በክልሉ ተግባራዊ እየሆነ በመሆኑ መረጃዎችን በታማኝነት በመመዝገብ ወቅታዊ ሪፖርቶችን በመላክ ረገድ ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት ይጠበቅበታል።
የመድረኩ ተሳታፊ ባለድርሻ አካላት የምግበ ሥርዓት እና ሥርዓተ ምግብ ተግባር የማህበረሰቡ የአመጋገብ ዘይቤን በመቀየር በምግብ እጥረት ምክንያት የሚከሰቱ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ ሚናው የጎላ በመሆኑ ለውጤታማነቱ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡም ተናግረዋል።
በሚዛን አማን ከተማ በተካሄደው የመጀመሪያ ዙር መድረክ የዳውሮ፣ ኮንታ እና የምዕራብ ኦሞ ዞን የብዝሀ ሴክተር ቁልፍ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን ቀጣይ ቤንች ሸኮ፣ ሸካና የካፋ ዞን ባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ ምክክር መድረክ በሚቀጥለው ዙር እንደሚደረግም ተገልጿል።
በፍቅር ከበደ
