
በክልሉ ነባር የአዉሮፕላን ማረፊያዎች ወደ ሥራ ለማስገባት የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንዲሚቀጥልም ተገልጿል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከዚህ ቀደመ አገልግሎት ይሰጡ የነባሩና በተለያዩ ምክንያቶች አገልግሎት ያቋረጡ የአውሮፕላን ማረፊያዎችን ዳግም ወደ ሥራ ለማስገባት የተጀመረው ጥረት ተጠናክረው እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ አበራ እንደገለጹት፥ በክልሉ ከዚህ ቀደመ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ ለአብነት፥ የታርጫ እና የማጂ ቱም የአውሮፕላን ማረፊያዎችን ዳግም ወደ ስራ ለማስገባት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የባለሙያ ቡድንን ወደ ስፍራው እንደሚልክ አስታውቀዋል።
የቦንጋ ቀላል የአዉሮፕላን ማረፊያ ግንባታው የተጓተተ በመኾኑ በትኩረት በማጠናቀቅ ወደ አገልግሎት ለማስገባት ጥረት እንደሚደረግ የተናገሩት አቶ ዮሐንስ በክልሉ ውስጥ ሌሎች ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ተከትለው የተገነቡ ቀላል የአውሮፕላን ማረፊያዎችንም በመጠገን ወደ ሥራ እንዲገቡ ይሰራል ብለዋል።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የቀላልና አነስተኛ የአውሮፕላን ማረፊያዎችን በሀገሪቱ ለማስፋፋት በተዘረጋው አሰራር መሠረት የቴፒ አውሮፕላን ማረፊያ ዳግም ወደ ስራ መግባቱን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፥ የአካባቢው መንግሥት የተሰጠውን የማሻሻያ ሀሳቦች በአጭር ጊዜ ተግባራዊ በማድረግ ለአገልግሎት ማብቃት መቻሉ ለሌሎች ምሳሌ የሚኾን እንደሆነ ተናግረዋል።
የሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ የግንባታ ሁኔታ በተያዘለት ጊዜ በጥሩ የግንባታ ጥራት እየተከናወነ እንደሆነ የገለጹት አቶ ዩሐንስ እስከ ቀጣይ አመት አጋማሽ ግንባታው ተጠናቀው ለአግልግሎት ክፍት እንደሚኾንም አስታውቀዋል።
አየር መንገዱ ገበያ መር የኢኮኖሚ ፖሊስን የሚከተል በመኾኑ የአዋጭነት ጥናቶችን በየጊዜው እያደረገ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚያስፋፋ ያብራሩት ዋና ዳይሬክተሩ ከዚህ ቀደም ክልሎችን ከአዲስ አበባ ጋር ማገናኘት ትኩረት ያደረገው አሰራር አሁን ላይ ክልል ወደ ክልል የማገናኘት ስራ ላይ ማተኮሩን ነው የገለጹት።
በዚህም የአየር ትራንስፖርት መዳረሻዎችን በማስፋፋት ቀላልና ፈጣን የትራንስፖርት አግልግሎት በማቅረብ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ለውጥ ለማፋጠን ይሰራል ብለዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ለሀገር ዕድገትና ብልጽግና መረጋገጥ ጉልህ ሚና የሚጫወት የኢኮኖሚ አቅሞች ያሉበት አንዱ የኢትዮጵያ ክልል መኾኑን የገለጹት አቶ ዮሐንስ የህንን ሀብት በቀላሉ ወደ ገበያ ተደራሽ በማድረግ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የአየር ላይ ትራንስፖርት በጥራትና በብዛት ማስፋፋት ተቀዳሚ ተግባር እንደሆነ ተናግረዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
